የእግዚአብሔርን ጉብኝት ተርባችኋል?

ጄምስ ጎል :

በሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር ከመገናኘት በላይ አስፈላጊ የሆነ ልምምድ የለም። ከእርሱ ጋር አንድ ጊዜ መገናኘት ሕይወታችንን ሁሉ ነው የሚቀይረው። ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች ይቀየራሉ፤ እይታችን ይቀየራል፤ በጣም አስፈላጊ ናቸው እንላቸው የነበሩ ነገሮች ወደ ኋላ ይቀራሉ። ድንግዝግዝ የነበረው ሕይወታችን በብርሃን ይሞላል።

የእግዚአብሔርን ጉብኝት ተርባችኋል? ሕይወታችሁን መጥቶ እንዲቆጣጠረው ትፈልጋላችሁ? በ1992 እግዚአብሔር ባለቤቴን የጎበኝበትን ጊዜ መቼም አልረሳውም። ከዛ በኋላ ሕይወቷ እንደነበረው አልቀጠለም።

ምንም እንኳን በ2008 ካንሰር የሚሸል አንን ስጋ ቢነጥቅም፤ አሁን እሷ በጎበኛት አምላኳ ህልውና ውስጥ ትኖራለች። አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን እግዚአብሔርን እንደገና በሃይል ለመራብ የሌሎች ምስክርነት አስፈላጊ ይሆናል። ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የሚሸል አንን የምስክርነት ቃል እግዚአብሔር በሕይወታችሁ እሱን ለማግኘት ያላችሁን ረሃብ ይቀስቅስበት።

ሚሸል አን ጎል የእግዚአብሔር ጉብኝት ምስክርነት

ጀምስ ከፊት ለፊቴ “ቆሞ ጨርሶ የማላውቃት ሴት ሆነሽብኛል፤ ምን እየሆንሽ እንደሆነም አላውቅም”። ያለኝን ያንን የ1992 ሕዳር ወር ምሽት መቼም አልረሳውም። እኔም መልሼ “እኔም እራሴ በሕይወቴ ምን እየሆነ እንዳለ አልውቅም” ነበር ያልኩት። ነገሩ ጭራሽ በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል እንጅ ለ16 አመታት በትዳር በቆዩ እና 4 ልጆችን ወደዚህ አለም ባመጡ ባል እና ሚስት መካከል የሆነ አይመስልም ነበር። ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ምክንያቱ በዛን ምሽት የእግዚአብሔር ጉብኝት በአስደናቂ ሁኔታ ሕይወቴን እየቀየረኝ ስለነበር ነው።

በታሪክ ውስጥ መለኮታዊ የሆነው የእግዚአብሔር ጉብኝት የተራ የሰዎችን ሕይወት እስከ መጨረሻው ሲቀይር አይተናል። መለኮታዊ ጉብኝት ስል የእግዚአብሔር ህልውና በእኛ ሁኔታዎች እየተገለጠ ሕይወታችንን የተቆጣጠረባቸውን ጊዜያት ማለቴ ነው። መጥቶ ማንነቱን ይገልጣል፤ ባህሪውን፣ ሀይሉን፣ ፍቅሩን ባጭሩ ራሱን ይገልጣል። ይህን አይነት ጉብኝቶች በግለሰብ ሆነ በብዙዎች ሕይወት በትውልድ እና በሃገር ደረጃ ሲከሰቱ ሁልጊዜ ይዘውት የሚመጡት ነገር አለ ይህውም ለታለቁ አምላካችን ያለንን ንቃተ ህሊና ከፍ ያደርጉታል።

ብዙዎች እግዚአብሔር በዛ ምሽት ከጀመረው ጉብኝት በኋላ በሕይወቴ ለውጥን አስተውለዋል። በዛን ወቅት የተነሳነው የቤተሰብ ፎቶ አለ፤ ሰዎች እነዛ ፎቶዎች አዲስ ሀይል ሰማያዊ የሆነ እና ከዛ የእግዚአብሔር ጉብኝት በፊት ያልነበረ ማንነትን ያሳያሉ በለው ያምናሉ። ከእግዚአብሔር ጉብኝት በኋላ ሙሉ ሕይወቴ ለዘለዓለሙ እንደተቀየረ እኔ እራሴ በመረዳት ልነግራችሁ እችላለሁ።እግዚአብሔር አምላክ ቤተ  ክርስቲያኑን በተመሳሳይ መጎብኝት ይፈልጋል። ለሙሽራው ያለዉን ቅንዓት በግልጽ ሊያሳይ ይፈልጋል፤ ታላላቆቹን እና ታናናሾቹን፣ ተናጋሪውን እና ዝምተኛውን፣ ደፋሩን እና አይን አፋሩን ሕዝቡን ሁሉ ከእርሱ ጋር ባለው ጠንካራ ሕብረት ላይ ወደ ተመሰረተ አገልግሎት ማስገባት ይፈልጋል። ወደዚህ ጥልቅ ሕብረት ለመግባት ራሳችንን መስጠት ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል።

ከእርሱ ጋር ጥልቅ ወደሆነ ሕብረት እንድንገባ ጌታ እግዚአብሔር ደጋግሞ ይጋብዘናል። ወደዚህ የሕብረት ስፍራ ነው መገስገስ የሚያስፈልገን፤ ይህን የምናደርገው ጌታም እራሱ ወደ እኛ እየገሰገሰ ስለሆነ ነው። የወንጌሉ ሚስጥር ዘመን የማይሽረው መለኮታዊ የፍቅር ታሪክ ሚስጥር ነው፤ ከምንም ነገር በላይ ሊፈርስ ወደማይችል ሕብረት ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር እስክንሆን ድረስ ልባችንን እየማረከ እኛን ወደራሱ የሚስብበት። በመንፈስ መመላለስ የአእሞሮ እውቀት ጉዳይ አይደለም፤ የሙሽራውን ጥሪ የመስማት እና ለጥሪውም የልብ መልስ የመስጠት ጉዳይ እንጅ። እግዚአብሔር ሙሽራይቱን ወደራሱ እየጠራ ስለ እርሷም እየተዋጋ ነው። ሙሽራይቱን የወደዳት በታላቅ ፍቅር ነው፤ ከእኛም እየጠየቀ ያለዉ ነገር የእርሱ ነጸብራቆች እንድንሆንለት ነው። እግዚአብሔር ለእርሱ በቅንዓት የምንዋጋ፣ በሙሉ ልባችንም የምንወደው ሕዝቡ እንድንሆንለት ይፈልጋል።

የጉብኝታችንን አምላክ የምንፈልግበት እርሱም ደግሞ በኋለኛው ዝናቡ ምድርን የሚያጠጣበት ጊዜው አሁን ነው። ሰውን የእውነት ስትወዱ እና ሙሉ ልባችሁን ስትሰጡት ለእርሱ የማታደርጉት ምንም ነገር አይኖርም፤ ምንም ነገር ማድረግ ከባድ አይሆንም።የእግዚአብሔር የጉብኝቶቹ ሁሉ ዓላማ እሱን የበለጠ እናውቀው ዘንድ ነው።

እግዚአብሔርን ምሰሉ የሰጣችሁንም ፍቅር ለሌሎች ስጡ! ብዙ ከተቀበላችሁ ብዙ መስጠት ይጠበቅባችኋል! ያለውን ሁሉ ለሰጠን ጌታ ያለንን ሁሉ የምንሰጥበት ጊዜው አሁን ነው። ይህን የጉብኝት አምላክ በመፈለግ በእርሱ መጎብኝት ይሁንላችሁ! ይህ ትንቢታዊ የሆነው መለኮታዊ ሃይል ያግኛችሁ ይቀይራችሁም።ይህ ምስክርነት በሕይወታችሁ እሳትን አቀጣጥሏል ብዪ ተስፋ አደርጋለሁ።

Download Here

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox