በመንፈሱ ቅብዓት እየረሰረሳችሁ ነው?

ጄ. ሊ ግሪዲ ፡

ጊዜን የኋሊት ተጉዛችሁ የመገናኛውን ድንኳን ማየት ብትችሉ በቅጽበት ትኩረታችሁን የሚስበው መቅደሱን በመኣዛ የሚያዉደው የቅብዓት ዘይት ነው። በድንኳኑ ውስጥ ያለ እቃ ሁሉ በዚህ ቅብዓት የረሰረሰ ነበር። ይህ ንጥር ቀረፋ፣ ከርቤ እና ሌሎች ቅመሞችን ከወይራ ዘይት ጋር በመቀላቀል ነበር የሚዘጋጀው።

በዚያ ቅዱስ ቦታ ያለ ነገር ሁሉ በቅብዓቱ ዘይት እንዲቀባ እግዚአብሔር አምላክ ሙሴን አዞት ነበር፤ ድንኳኑ፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ ገበታው፣ መቅረዙ፣ የእጣን መሰዊያው፣ የመታጠቢያው ሳህን እና ማስቀመጫው፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሰዊያ እና እቃውንም ሁሉ እንዲቀቡ እግዚአብሔር አምላክ ተናግሮ ነበር። (ዘጽ 30 ፥ 26 – 28)

ካሕናቶችም እንዲቀቡ እግዚአብሔር ሙሴን አዞት ነበር። (ዘጽ 30 ፥ 30) በድንኳኑ ውስጥ ያለ እቃ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ሊገባ ያለ ማንም ቢሆን በቅዱሱ ቅብዓት መቀባት ያስፈልገው ነበር። 

ቤተክርስቲያን አሁን ያንን የመገናኛ ድንኳን ተክታለች። በዚህ የአዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሰው በሰራው ቅባት ሳይሆን በቅዱስ መንፈሱ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ሃይል እንድትረሰርስ ይፈልጋል።

ዛሬ ይህን በብዙ ቤተክርስቲያናት አናይም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ ያንን ቅብዓት አትረፍርፎ እንዲያዘጋጅ ነብር ያዘዘው። ዛሬ ዛሬ በመሰዊያዎቻችን ላይ የምናስቀምጣቸው ትናንሽ የዘይት ብልቃጦች ለቅባቱ ያለንን ትንሽ ስፍራ የሚያሳዩ ናችው። በትንሽ ወይም በባዶ ዘይት ረክተናል። ደርቀናል አቅምም ደግሞ የለንም።

በወጣትነት ዘመኔ በመንፍስ ቅዱስ ከተሞላሁበት ጊዜ ጀምሮ ኤፌሶን 5 ፥ 18 በህይወቴ ትልቅ ስፍራ አለው፤ እንደዚህ ይላል ፥ “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጅ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና።” እግዚአብሔር ቅባቱ በህይወታችን ሞልቶ እንዲትረፈረፍ ይፈልጋል። መረስረስ እየቻላችሁ ስለ ምን ትደርቃላችሁ?ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን በሙላት እንዳይሰራ የሚከለክሉ ስድስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ።

  1. ተጠራጣሪነት እና አዉቃለሁ ባይነት ፥ በአለም ዙሪያ በተደጋጋሚ ስጓዝ ያስተዋልኩት አንድ ነገር ቢኖር ብዙ አልተማሩም የምንላቸው ሰዎች የመንፍስ ቅዱስን ስራ ለመቀበል ቅርብ መሆናችውን ነው። በቅላሉ በልሳን የሚሞሉትም እንደዚህ አይነት ሰዎች ናችው። የተማሩ የተባሉት በእውቀታቸው ይደገፋሉ፤ መንፈሳዊ ልምምድ ደግሞ በጭንቅላታችን የምንተነትነው ነገር አይደለም። በመንፈስ ለመሞላት እንደ ህጻን የሆነ እምነት ያስፈልጋችኋል። (ማቴ 18 ፥ 2 – 4)
  2. ሐይማኖታዊ ወግ አጥባቂነት ፥ በ1970ዎቹ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በመንፍስ ቅዱስ የተሞላ አንድ ቄስ አውቅ ነበር፤ ይህ ሰው በእምነቱ ውስጥ ባገኘው በዚህ አዲስ ነገር አብዝቶ ይገረም ነብር፤ በአንድ ወቅት ባለቤቱ ከህመም ተፈዉሳም ነበር። ይህን ምስከርነቱን ለበላይ ካህኑ ሲያካፍል የተሰጠው መልስ አብድሃል የሚል ነበር። በለመድነው ብቻ እንሄዳለን በሚል እስራት ለተያዙ ሰዎች በመንፍስ መሞላት ጭንቅ ነው። ከሐይማኖት ወግ አጥባቂነት ነጻ መዉጣት አለባችሁ።
  3. የልዕለ ተፈጥሮ ፍርሃት ፥ አንዳንዶች ያደጉት የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን በሚቃዎም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። በመንፈስ ተሞልተናል የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን የሳቱ እና የሚናገሩትን የማያውቁ ለፍላፊዎች ናቸው ተብለው ነው የተነገሩት። በእርግጥ የአዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በልሳን ተናግረዋል ተዓምራትንም አድርገዋል፤ እምነታቸው ግን መጤ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ መጽሃፍ ቅዱሳዊ የእምነት ምሳሌን አስቀምጠውልን ነው ያለፉት።
  4. ንስሃ ያልገባንበት ሃጢያት ፥  መጽሃፍ ቅዱሳችን መንፈስ ቅዱስ ሊጠፋ እና ሊያዝን እንደሚችል ይነግረናል። (1 ተሰ 5 ፥ 19፤ ኤፌ 4 ፥ 30)። ለዚህም ነው ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ማድረግ እና ሃጢያት እንደሰራን ሲገባንም በቶሎ እንድንናዘዝ የሚያስፈልገን። በመንፈስ ለመሞላት ከፈለጋችሁ የልባችሁን ጓዳ መክፈት እና የእግዚአብሔር ቅድስና በእያንዳንዱ የሕይወታችሁ ጨለማ ጥግ ላይ እንዲያበራ መፍቀድ ያስፈልጋችኋል።
  5. የስሜት ቁስሎች ፥ አንዳንዶች በመንፈስ የማይሞሉት ሕይወታቸው በብዙ የስሜት ቁስሎች እና ሸክሞች በመሞላቱ ነው። አንድንዶች ጥቃት የደረሰባቸዉ፤ ሌሎች ጭንቀት የተጫጫናችው፤ ሌሎች ደግሞ ሃዘን ወይም ድብርት ያለባቸው ናቸው። ለነዚህ በመጀመሪያ የሚያስፈልጋቸው ፈውስ ነው። እነዚህ አልዓዛር ከሞት በተነሳ ጊዜ እንደተገነዘበት ባለ የትናንት ድሪቶ የተተበተቡ ናቸው። የእግዚአብሔርን ቅብዓት በሙላት ከመለማመዳቸው በፊት ከዚህ ነጻ መውጣት ያስፈልጋቸዋል። (ዮሐ 11 ፥ 44)። ብዙ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ከመጠመቅ በፊት ፈውስ አስፈላጊ ነገር ነው።
  6. ያልተሰጠ ማንነት ፥ ራሳችሁን ካልሰጣቸሁ በመንፈስ ልትሞሉ አትችሉም። አንዳንዶች በራሳቸዉ ዓለም ነው የሚኖሩት፤ እቅዳቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ግንኙነታቸውን እና ጊዜአቸዉን ለእግዚአብሔር አሳልፈዉ አልሰጡም።  እግዚአብሔር በሕይወታችው ጣልቃ እንዲገባም አይፈልጉም። እግዚአብሔር ለሱ የተሰጡ እና የተራቡ ልቦችን ሊሞላ ይፈልጋል። የሃይሉን ሙላት መለማመድ የሚችለዉ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ ሰዉ ብቻ ነው።

የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ካልተቀበላችሁ ወይም ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችሁ በሙላት እየሰራ ካልሆነ ልባችሁን ባዶ አድርጉ ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ራሳችሁን አዘጋጁ። እግዚአብሔር አምላክ ቅብዓቱ በሕይወታችሁ ሞልቶ እስኪትረፈረፍ ሊሞላችሁ ይፈጋል።

Download Here

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox