ከመአት የወጣሁ እህት

እህታችሁ ሰዓዳ መሀመድ ከጅቡቲ ብርሃን መፅሔት 1989 ቁጥር 27 :

ዕድሜዬ ከመማር በቀር ለሌላ ለምንም ነገር ሳይደርስ የጫት የሲጋራ እና የመጠጥ ተገዢ ሆንኩኝ፡፡ ከዚያም ዕድሜዬ ለአቅመ ሄዋን ሲደርስ ከቤተሰቦቼ ተለይቼ በሠይጣን ምሪት የመኖሪያ ስፍራዬን ቀየርኩ፡፡ ወደ ቡና ቤቶች መንደር አመራሁ ተዋናይም ሆንኩ፡፡ ከዚህ ሁኔታ በኋላም አይን አለኝ አላይም ጆሮ አለኝ አልሰማም፡፡ በምደርስበት አካባቢ ሁሉ የታወኩ ጠጪ ሆንኩ፡፡ ጠዋት እልል ማታ መጠጣትና መስከር የዘወትር ሥራዬ ሆነ፡፡ አእምሮዬ ሁሉ በመጠጥ ደነዘዘ ደሜ በአልኮል ተበረዘ፡፡ ዘወትር እሩጫዬ ኃይል ሰጪ የሆኑትን መጠጥ ሀሺሽ ሲጋራና ጫት ለመፈለግ ሆነ፡፡ ምክንያቱም ያለ ተጨማሪ ኃይል ለእኔ አንድ እርምጃ መራመድ የአቀበት ያህል ይከብደኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን የኃጢያት ኑሮዬንና እንደገናም የታወቅሁና የለየልኝ ጠጪ መሆኔን ሳስበው የኀዘኔንና የለቅሶዬን ልክ በቃላት ልገልፀው ይቸግረኛል፡፡ አዎ! ዛሬ ዛሬ ግን ደስ ይለኛል፡፡ ያ የኀዘንና ለቅሶ ዘመኔ አልፏል፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!

ነፍሴ ግን ከኃጢያት ኑሮ የሚገላግላትና ከሱሶች ሁሉ ነፃ የሚያወጣትን እውነተኛ አምላክ ትሻ ነበርና ዘወትር ታስጨንቀኝ ነበር፡፡ እኔ የግዚአብሔርን መኖር ከማወቅ በስተቀር በግሌ ሃይማኖትም ሆነ የግል አምላክ አልነበረኝም፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ሱማሌዎች ነበሩና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ እኔም ከጭንቀቴ ይገላግለኝ አንድ ወደ ቤተሰቦቼ አምላክ ወደ አላህ ጩኸቴን አሰማሁ፡፡ የቤተሰቦቼን አምላክ እባክህን ካለሁበት የኃጢያት ኑሮ ገላግለኝ በእነዚህ ሁሉ ሱሶች ታስሬያለሁና አንተን በመፍራትም እንድኖር እርዳኝ ብዬ ለመንኩኝ ነገር ግን ምንም መልስ አልነበረም፡፡እኔ በዚያን ሰዓት ስለኃጢያቴ ነፍሱን በቀራንዮ ላይ አሳልፎ የሰጠውን ውዴን የናዝሬቱን ኢየሱስን አላውቅም ነበር፡፡ ጥያቄዬን የሚመልስ እንቆቅልሼን የሚፈታ ከዘላለም ሞት ነፍሴን የሚታደጋት የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነበር፡፡ የሚያድን ሃይማኖት የቤተሰብ አምላክ የተለያየ አምልኮ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታ ሌላ የለምና›› (የሐዋ.4፤12)ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ አእምሮዬ ስለሚያውቅ ነፍሴ በብዙ ትጨነቅብኝ ነበር፡፡ እንግዲህ እኔም ከቤተሰቦቼ አምላክ መልስ ስላላገኘሁ ወደ ሌሎች ወደ ሌሎች አማልክቶች መሄድ ግድ ሆነብኝ፡፡ ስሄድ ስሄድ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ነን እያሉ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ክቡር ሰው የፈረስ ስም ሰጥተው በሰዎች ላይ ሆነው ወደሚናገሩ መናፍስቶች ጋር ደረስኩ፡፡

በመጀመሪያ እኔ ወደ እነርሱ ስሄድ የማቀውንና የማላውቀውን የሕይወት ታሪኬን እየነገሩኝ እንዳምናቸው አደረጉኝ፡፡ እምነቴ ግን የጥርጥር ነበር፡፡ እጃቸው እስከምገባ እንደምንም ካግባቡኝ በኋላ አርግዤ የነበረውን የ7ወር ጽንስ እንዳስወርድ አዘዙኝ መንገዱንም ጠቆሙኝ፡፡ ከውርጃው በኋላ ደግሞ እንዲያስተውኝ የለመንኳቸውን መጠጥ ደግሞ እንዳቆም በግድ ሲያስገድዱኝ ጭራሹን አደገኛ የመጠጥ ሱሰኛ ሆኜ አረፍኩት፡፡ በጠጭነት የመኖር ህልውናዬ ሁሉ ስለተናጋ እነዚህኑ መናፍስቶች መማጸን ጀመርኩ፡፡ እነርሱ ግን እንኳንስ ሊያስጥሉኝ የመጠጥ አይነቶች መስሪያ ጋን አድርገውኝ ቁጭ አሉ፡፡ እኔም በየጊዜው ስለትን መሳል ሥራዬ አደረኩት ስለት ተስዬ ስለቴ ባይደርስም የተሳልኩትን ወስጄ ስለማምን ደግሞ ይህች እስላም ያለ ሃይማኖቷ እየጠጣች ነውና ካልሰገደች የእስላም ፆም ካልፆመች አንፈውሳትም ሲሉ ደግሞ አንድ ሰሞን እስላም ሆንኩ፡በዚያኑ ሰሞን እስልምናዬን ሳስታሰው ይገርመኛል ያስደንቀኛልም፡፡ አጋንንት በሰው ጊዜ የመጫወቱ ነገር ያስደንቀኛል፡፡ እኔ የማላውቀው ነገር ግን መጠጥ እንድጠጣ የሚገፋፋኝ አንድ ኃይል በውስጤ ነበር የጠጣው ቀን ደግሞ ያው በሰው ተጠቅመው ብዙ የመግደል ሙከራ አድርገውብኝ ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ ምክንያቱም ከዘመናት በፊት ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ የመረጠኝ ልዑል እግዚአብሔር ነፍሴን ብቻ ሳይሆን ሥጋዬንም ጭምር ይታደግ ስለነበር ነው፡፡ እንግዲህ የአጋንንት ነገር ጉዱ እያደር ነውና እኔ ሳልፈቅድ ስለት ተሳይ ማለት ጀመሩ፡፡

እዚያ እኔ የማመልክበት ሥፍራ ብዙ ሰዎች ይመጣሉ ስለት ያላመጡለትን ሰዎች ስለቴን ገንዘቤን በልታችኋል እያለ በቁስል በበሽታ በድኅነት ሲመታ ሳይ እንዴ እኔንማ እንደዚህ ልታደርገኝ አትችልም ምክንያቱም ምንም ስላልሰጠኸኝ ምንም ላደርግልህ አልችልም ምናልባር እንኳን ለማድረግ ብትሞክር አንተም ትሞታለህ እኔም እሞታለሁ እግዚአብሔር ፊት ግን ለፍርድ እኩል እንቆማለን እለው ነበር፡፡ ታዲያ እሱ መንፈስ ስለሆነ ይህንን በውስጤ ማለቴን ስለሚያውቅ አንቺ ሰው እመኚኝ ልብሽን ስጪኝ ይለኝ ነበር፡፡ እውር እያበራህ ሽባ የተረተርክ የእገሌ ጌታ በይኝ ሲለኝ እኔ ደግሞ የታለና ሲበሩ እና ሲተረተሩ ያየሁት እያልኩ ራሴን በጥያቄ አስጨንቀው ነበር፡፡ ታዲያ እንኳንስ ያላየሁትን እውር በራ ብዬ ላምነው ቀርቶ የራሴ ሕይወት ሁኔታ ትሻልን ትቼ ትብስን….. ሆኖብኝ ስጋት ላይ ወድቄያለሁ፡፡ እንዳልርቀው ዛቻውን ፈራው እንዳልቀርበው የሕይወት ለውጥ የለ ዝብርቅርቄ ወጥቶ አረፍኩት፡፡

እነዚሁ የእግዚአብሔር መልእክተኞአች ነን የሚሉኝ መናፍስቶች አንዴ የሚጠጣ፣ አንዴ የሚጨስ፣አንዴ መታጠቢያ ስራስር ወደ ሚሰጡ ሰዎች እየላኩኝ ነፍሴን ብክንክን አደረጓት፡፡ እኔም የሥራስርና የጽሕፈት መአት ተሸክሜ በተዘበራረቀ ሁኔታ ያልተረጋጋና በጥያቄ የተሞላ አእምሮ ይዤ ጉዞዬን ወደ ጅቡቲ አቀናሁ፡፡ የማልረሳው ነገር ግን ወደ ጅቡቲ በምሄድበት ሰሞን እኔን መጠጥ ለማስተው የገበታ ብለው ረከቦት ላይ የሚቀመጥ ገንዘብ ነው በማለት ያስከፈሉኝ 300.00ብር ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ከሡስ ነፃ ለማውጣት ጉቦ፤ዲያቢሎስ እንደው ምህረትን አያውቅ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል እግዚአብሔር የልቦናን አይን ካላበራ አንዳችም መመልከት አይቻልም፡፡ ከዚያም በኋላ ምን አለፋችሁ ጅቡቲ ከገባሁ በኋላ ጥሩ የጫት ወፍጮ ቤት ሆንኩ፡፡ ሲጋራማ የማይቆም ነገር ሆነ፡፡ ጫቱም እህል ሲጋራውም ማብሰያ ማገዶ ሆነው አረፉት፡፡ አንዳንዴ ወደ ማስተዋሌ ስመለስ የወለድኩባትን ቀን እረግም ነበር፡ግራ ከመጋባቴ የተነሳም በፊት አመልክበት ወደ ነበረው አገር ለመናፍስት ጠሪዎች ደብዳቤ መጻፍ ጀመርኩ፡፡ የመጀመሪያውን ደብዳቤ አሞር ገላጭ ለሚባለው መንፈስ ስጽፍለት ‹‹ ደብዳቤሽ ደርሶኛል አትቸኩይ፡፡ አንቺ ትቸኩያለሽ የቸኮለች አፍሳ ለቀመች ሲባል አልሰማሽምን?››ብሎ መለሰልኝ በሁለተኛው ደብዳቤዬ መልስ ላይ ደግሞ ያንቺን ጉዳይ የያዘው የገናሌው አዳል ሞቴ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በነበረን ስብሰባ ያንቺን ጉዳይ አንስቼ ስንወያይ ጉዳይሽን የያዘው አዳል ሞቴ እሷ ስለቴን በልታለችና ስለቴን ካላስገባች በቀር የእርሷ ጉዳይ የታሰረ ስለሆነ በመጀመሪያ ስለቴን ታምጣና ትመረቃለች ብሎሻል ብሎ አሞር ገላጭ የሚባለው መንፈስ መልስ ላከልኝ፡፡ ከዚያም እናቴን አስጨንቄያት የስለት እቃዎችን አስገዝቼ አመልክበት ወደነበረው አገር ሄድኩ፡፡ ከዚያም ስደርስ ልዩ አቀባበል ተደረገልኝ፡፡ የሚፈርጥ እንቁላል፣የሚሰበር ብርጭቆ አደረጉኝ፡፡ መስተንግዶው መሬት አይንካሽ ከአልጋ አትውረጂ ሆነ፡፡ እንኳንስ የሰዎቹ የመንፈሱም የቅርብ ሰው ሆንኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ መቸም ያው መቆየት የሚያስከትለው ነገር መጣ፡፡ አንድ ወር ገደማም እንደቆየሁ ገንዘቤ አለቀ፡፡ እነርሱም አንቅረው ተፉኝ፡፡ እኔም ወደ መጣሁበት ተመለስኩ፡፡

እንደገና በድሬደዋና በሐረር የአጋንንት አምልኮዬን ቀጠልከኩ፡፡ አንድ ቀን ሐረር ለአምልኮ ሄጄ ጫት ስንቅም አመሻሸንና ሌሊት ላይ ወሰን ጋራ የሚባለው መንፈስ በሴትየዋ ላይ ወረደና መፎከር ጀመረ፡፡ እግዚአብሔር ዓይኔን ከፍቶልኝ ስለነበር የሚለውን ነገር ሁሉ በተመስጦ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ከዚያም መፎከር ጀመረ፡፡ እኔ በሰማይ በራሪ በምድር ተሸከርካሪ ጋራለጋራ ተዘዋዋሪ በአየር ተምዘግዛጊ ዝሆን ጋላቢ አንበሳ ገሪ አለና ቆንጆ ቀሳፊው ሲል ከአእምሮዬ ጋር መነጋገር ጀመርኩ፡፡ ለምን?እንዴት? ቆንጆ ምን አደረገና ይቀሰፋል? በማለት ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምን፡፡ ከዚያ እኔን ቡዳ በልቶሻል ብሎ ከነገረኝ በኋላ የበላሽን ቡዳ አሁን አስወጣለሁ አለኝና እኔን ወደ መሀል አስገብተው ጫት ሲተፉብኝ ከቆየ በኋላ ማነህ አንተ ውጣ እያለ ግንባሬን ብዙ ቀጠቀጠኝ፡፡ በጣምም አመመኝ፡፡ ከዚያ ውጣ እኮ ነው የምልህ አንተ ማነህ ማለት ሲያበዛ እኔ ሰዓዳ ነኝ አልኩት፡፡ በእኔ ላይ ሆኖ የሚናገር ሌላ መንፈስ አልነበረም፡፡ ከዚያም በመኩራራት ውጣ ብሎ ከጮኸ በኋላ አጠገቤ ቆሞ ለነበረው ሐጅ ሂድና ጦሬንና ጎራዴዬን አምጣ ሲለው አንገቴን ቀንጥሰው እንዳይጥሉት ብዬ ሰጋሁ፡፡ በኋላ ግን ምንም ነገር ሳይመጣ ቀረ፡፡ የወጣም ነገር አልነበረም፡፡ ጉዳዩ በቀጠሮ ተላፎ ሲቀር እኔ በጥያቄ ተሞላሁ፡፡

የእግዚአብሔር መልእከተኛ ከሆነ ለምን ቡዳውን አልያዘውም ልመናው ለምን አስፈለገ? ማለት ጀመርኩ፡፡ ድሮውንም እምነቴ ጥርጥር ነበርና የባሰውኑ ቀነሰ፡፡ ታዲያ በዚሁ የሀረር ቆይታዬ እግዚአብሔር ብዙውን የአጋንቶች አሰራር አስተማረኝ፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡ ከዚያም እኔም ወደ ጅቡቲ ተመለስኩ፡፡ በፊት ቡና የማፈላው ረቡዕ ቀን ነበር፡፡ ከተመለስኩ በኋላ ግን እሁድ ማፍላት ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም የያዘሽ የእስላም ሳይሆን የክርስቲያን አወሊያ ነው ስላሉኝ ነበር፡፡ እኔም ታዲያ ትንሽ እሁዶች ካፈላላሁ በኋላ የማመልካቸው አማልክቶች አሠራር ውሸት ውጤት አልባነት ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ የማውቃቸው አማልክቶች ብዛት ነፍሴን አስጨነቋት፡፡ ሕሊናዬ ተናጋ፡፡ የመኖር ትርጉሙ ጠፋኝ ለማንና ለምን እንደምኖር ማወቅ ተሳነኝ፡፡ ነገ እኔም ተነስቼ ትንሽ አምላክ እንዳልሆን ስለሰጋሁ ወደ እግዚአብሔር ፀለይኩ፡፡ እርሱም ፀሎቴን ሰማ፡፡ ወዲያውኑ የማመልክባቸውን ነገሮች በኢየሱስ ስም እያልኩ ጣልኳቸው፡፡ ጌታንም አልተቀበልኩም ነገር ግን ለሠይጣን በአንደበቴም በልቤም የኢየሱስን ጌትነት ነገርኩት ውሸታምነቱንም አስታወቅሁት፡፡ እንደማልፈልገውም እንደማላመልከውም ነገርኩት፡፡እርሱም ሰማ ሰይጣንም ተናደደ፡፡ ከዚያ ብዙ ሊያስፈራራኝ ሞከረ፡፡ እኔም ጌታን ሳላውቅ በኢየሱስ ስም እያልኩ አስፈራራው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጠላት ዲያቢሎስን አላስፈራራውም፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡ የስሙንም ስልጣን ስላወቅሁ ስለተረዳውም አዘዋለሁ፡፡ በኢየሱስ ስምም ዕቅድ አላማውን ሀሳብና ምክሩን ሁሉ አፈራርሳለሁ፡፡ የኢየሱስ ስምም ለዘላለም ይባረክ፡፡

ገና በኃጢያት በነበርኩበት ጊዜ የእርሱን ውሸታምነትና ምንም ማድረግ እንደማይችል ለብዙዎች እመሰክር ነበር፡፡ ሠይጣንም ብልህ ስለሆነ እጄን ለጌታ እንዳልሰጠሁና የእርሱንም ስራ እንደምሠራ ስላየኝ ሆዴን አሳብጦ ሊገለኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ጫቱ እና ኮካው ሆዴን ያሳበጠኝ መስሎኝ ማታ ማታ ስተኛ ሆዴን የማስርበት መቀነት አበጀሁ፡፡ እሱ መች መቀነት የሚያግደው መች ሆነ፡፡ የሚያግደው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ስለነበር እግዚአብሔርም በፍቅሩ ስቦኝ አባብሎኝ ወደ ቤቱ አመጣኝ፡፡ ከዚያም አንድ ቀን የቤተክርስቲያናችን ሽማግሌ ወደ ሆነው አንድ ወንድም ቤት ሄጄ ስለ ኢየሱስ እና ስለመንፈስ ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ ንስሐ ገብቼ ወደ ቤት ለመመለስ በመንገድ ላይ ሳለሁ አሁን ሲጋራ እንዴት አጨሳለሁ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቄያለሁ? እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ወደ ሕይወቴ የጋበዝኩት ኢየሱስ ግን ሕይወቴን በሰኮንድ ውስጥ ለወጣት፡፡ እኔ በቀድሞ ኑሮዬ እንደክብሬ የማወራ ዓይን እያለኝ የማላይ ጆሮ እያለኝ የማልሰማ ሰው ነበርኩ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን ሠይጣን ለአሥራ ዘጠኝ ዓመታት ሲያስምገኝ የነበረውን የማጨስን ነውርነት ገለፀልኝ መታዘዝንም አስተማረኝ የእግዚአብሔር ፍርሀት በእኔ ላይ ወደቀ፡፡ ከዚያ በኋላማ መቼ የጌታን ቃል አጣጥሜ በልቼ ጌታን ለማያውቁ ይህን የእውነት አምላክ ይህን ፈዋሽ አምላክና ይህን የዘላለም ሕይወት ሰጪ ኢየሱስን ነግሬ የሚለው መሻት በውስጤ ነደደ፡፡ የልቤ ናፍቆት በአንድ በኩል ሲቀጣጠል በሌላ በኩል ደግሞ ቤተክርስቲያን ለአምልኮ ስሄድ ሰባኪው ያልዳኑትን ወደ ጌታ እንዲመጡ ሲጋብዝ እኔ በንዴት ብግንና እርር እል ነበር፡፡ የሚድኑ ሰዎች በጠፉ ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎኝ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ፡፡ ወንጌል ሰባኪ መሆን እየፈለግሁ እንደገና ደግሞ ነፍሳት ሲድኑ መበሳጨቱን ሳስበው እገረም ነበር፡፡

በጣም የሚገርመው ታዲያ እስከ መጨረሻው ሰዓት ማለትም እስከ ተፈወስኩበት ቀን ድረስ የአጋንንቶች ማደሪያ ዋሻ መሆኔን አላውቅም ነበር፡፡ በቀን ቢያንስ ከአስር ጊዜ በላይ እቀያየር እንደነበር ይህንን አውቅ ነበር፡፡ ከዚያም ገና የአራትወር ክርስቲያን ሳለሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ላይ ሆነን ስለመንፈስ ቅዱስ ሙላት ስንልይ ወገኖቼ መንፈስ ቅዱስን ሲሞሉ እኔን ደግሞ አጋንንት በራሱ ኃይል ሞላኝ፡፡ በሁለተኛው ቀን ደግሞ በምሽት የፀሎት ፕሮግራማችን ላይ የሐሰት ልሳን ሰጠኝ፡፡ ከዚያማ በውስጤ የሞላው የአጋንንት ኃይል ስለሆነ ያገኘሁትን ሰው ሁሉ እንዳጋጨው ያዝዘኝ ነበር፡፡ የሚጠጋሽን ይዘሽ አንዴ ብታሳርፊበት ይሰባበራል በውስጥሽ ያለው ኃይል መንፈስ ቅዱስ ነውና ሲለኝ የልዑል አምላክ የእግዚአብሔር ጥበቃ እጅግ በዝቶልኝ ስለነበር ማንንም ሳልደበድብ ቀረሁ፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ባርያውን መጋቢ ሰይፉ ከበደን ከአሜሪካ አገር ወደ ጅቡቲ ላከልኝ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቼ ነበርና በመጀመሪያው ቀን ፕሮግራም ላይ ነፍሴ ተጨነቀች የማየውን ነገር ቀርቶ እራሴንም ክፉኛ ጠላሁት በሁለተኛው ቀን ግን ወደ ፕሮግራሙ ከመሄዴ በፊት ግን ከጭንቀቴ የተነሳ የማደርገውን ሳጣ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ፀለይኩ፡፡ እግዚአብሔር ሆይ እኔ ልጅህ ክርስቶስ ኢየሱስ የተሰቀለለትንና የሞተለትን ህዝብህን ጠልቼ በውኑ አንተን መውደድና ማምለክ እችላለሁን? ጥላቻንም በልቤ አምቄ መፀለይ ከቶ አይሆንልኝም ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ እኔ አለምንና ሠይጣንን ክጄ ወደ ቤትህ መጥቻለሁና እንግዲህ ብትሠብረኝም ብትጠግነኝም የአንተው ነኝ እኔ ከአንተ ሌላ አምላክ አላውቅም እባክህን ፈውሰኝ ብዬ ፀለይኩና የሁለተኛውን ቀን ፕሮግራም ልካፈል ከቤቴ ወጣሁ፡፡

ከዚያም ከስብከት በኋላ በጉባኤው ውስጥ ላለን አንዳንድ ሰዎች በጥላቻ ስለመሞላታችን መልእክት መጣ፡፡ ከዚያም መጋቢ ሰይፉ አንዲፀልይልን ጠየቁኝ የጥላቻው በሽታ የያዘንም ተነስተን ቆምን እሳቸውም ፀለዩልን እኔ ግን ከዚህ የጥላቻ በሽታ ስለመዳኔ በእምነት ተቀበልኩኝ እንጂ ፈውስ የሚባል ነገር ጭራሽ አልተሰማኝም ነበር እኛም ተቀመጥን እሳቸውም ጌታ የፈወሰንን ለምስክርነት ሲጋብዙን ብዙዎች ሲወጡ እኔ ግን አልወጣሁም ነበር ነገርግን የመጀመሪያዋ እህት ከጥላቻ ስለመፈወሷ ስትመሰክር እኔን አንድ የማላውቀው ኃይል ከመቀመጫዬ አንስቶ አመጣኝ ብዙዎቹ ለምስክርነት ወጥተው እያለ እኔን ከመሀል ጠርተው ጌታ ስላደረገልኝ ከጠየቁኝ በኋላ ልፀልይልሽ ብለው ገና ራሴን ያዝ ሲያደርጉኝ የክርስቶስ ኢየሱስን ስም ሊቋቋሙ የማይችሉ አርባ አጋንንቶች እየጮሁ ለጌታ እየተንበረከኩ እና እየሰገዱ ወጡ፡፡ የፈወሰኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ስሙ ለዘላለም ይክበር! ከዚያም በከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ መንፈስ ቅዱስ ተሞላሁ፡፡
ዛሬ በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመራሁ አባ አባት ብዬ የምጮኽበት የልጅነት መንፈስ ተቀብዬ ከሠይጣንም ባርነት ነፃ ለመውጣቴ በውስጤ የሚኖረው ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ እየመሰከረልኝ በአባቴ ቤት በነፃነት አመልካለሁ፡፡ ከአባቴም እጅ ሊነጥቀኝ የሚችል አንዳችም ኃይል የለም፡፡ በቀድሞው ሕይወቴ ብዙዎች ያውቁኛል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከአዲስ አበባ ምድር ሲያጡኝ አይ ሰዓዳ በቃ የደረሰችበትን የሚያውቅ ጠፋ ይሉ ይሆናል፡፡እኔ ግን በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትኩም፡፡ በጅቡቲ ምድረበዳ የአገኘሁትን ውዴን የናዝሬቱን ኢየሱስን አመልካለሁ፡፡ እናንተስ? ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ ከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ አኔም አሳርፋችኋለሁ›› (ማቴ.11፤28) ተብሎ በቃሉ እንደረፃፈ ሰላምን ወደሚሰጠው ጌታ ቅረቡ፡፡ እኔ እመሰክርላችኋለሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘሁት ሰላም ደስታ እርካታና እረፍት በብዙ ገንዘብ ሊገዛና ሊገመት የማይችል ነው፡፡ የልዑል የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን፡፡

እህታችሁ ሰዓዳ መሀመድ ከጅቡቲ
ብርሃን መፅሔት
1989 ቁጥር 27

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox