የወጣቱ ቢሮ – ስለአገልግሎቱ ምን ይላል? ከብርሀን መፅሔት

ከብርሀን መፅሔት :

ከቢሮው አስተባባሪ ጋር ከአቶ እንዳልካቸው ሳህሌ ጋር ነበር በቢሮአቸው ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተስተናግዷል፡፡

ብርሀን፡- የወጣት ለክርስቶስ ዳራና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ እንዳልካቸው፡- የኢትዮጵያ ወጣት ለክርስቶስ አገልግሎት እንቅስቃሴ የጀመረው አሁን ባለበት ሁኔታ ቢሮ ተቋቁሞና ቦርድ ተመስርቶ አልነበረም፡፡ በጥቅምት ወር 1983 ዓ.ም ከበርተን ወጣት ለክርስቶስ በሚስተር ኒክ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ
አበባ ይመጣል፡፡ በዚህ በአገር ቤትም በበጎ ፈቃደኝነት ይሰራ ከነበረው ከጂም ጉዲ ጋር በመሆን በኤስ.አይ.ኤም.35 የምንሆን ሰዎች ጠርተው እራእያቸውን አካፈሉን፡፡ መጋቢ ስለሺ ከበደ አስተባባሪ የሆነበት ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ከዚያም በየዓመቱ ኮንፈረንሶች በየቤተክርስቲያናቱ ማድረግ ጀመርን አገልግሎቱ ሁሉን አቀፍም ስለነበር ራእዩን ያመጡት ከአለም አቀፉ አገልግሎት ጋር አገናኙን የኢትዮጵያ ወጣት ለክርስቶስም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ሆነ፡፡ በዓለም አቀፉ ቢሮ መስፈርት መሠረት በ1986 ዓ.ም የቦርድ አባላት ተመረጡ ከዚያም ቢሮውን ካደራጀን በኋላ አስተባባሪ ፀሐፊ ልንመርጥ ችለናል፡፡ እንቅስቃሴው ግን ከቢሮውና ከቦርዱ መደራጀት በፊት ነበር የጀመረው፡፡ በጊዜውም የወጣት ለክርስቶስ መዘምራንና የወንጌል ሥርጭት ቡድኖች ተቋቁመው ነበር፡፡ ከቢሮው ምስረታ በተጓዳኝ የመንግስት ፈቃድ ማግኘት ያሉትን አገልግሎቶች ማጠናከርና አዳዲስ አገልግሎቶችን መጀመር ላይ ተሳትፈናል፡፡ እንግዲህ ከመዘምራኑና ከወንጌል ስርጭቱ አገልግሎት ሌላ የሥነ ጽሑፍና የካሴት አገልግሎት በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡ ሌላው ባሳለፍናቸው ሁለት አመታት ትኩረት አድርገን የሠራነው ታላላቅ የወንጌል ሥርጭቶችን ማካሄድና የወጣት ለክርስቶስን አገልግሎት አብረው ሊሄዱ ለሚችሉ አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ድርጅቶች ማስተዋወቅ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በሁለት ሀምሌ ወሮች በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ኮንፍረንሶች ያካሄድን ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪም በድሬዳዋ በመጋቢት 1988 የወንጌል ሥርጭት ተከናውኖ 345 የሚሆኑ ሰዎች ጌታን ተቀብለዋል፡፡ የወንጌል ሥርጭት አገልግሎቱም ተጀምሯል በቅርቡም ሄደን ሥልጠና ሰጥተን ተመልሰናል፡፡ በአጠቃላይ እንግዲህ ወጣት ለክርስቶስ በአለም አቀፍም ደረጃ አራት የአገልግሎት ዘርፎች ነው ያሉት እነርሱም ወንጌል ማሰራጨት ደቀ መዝሙር ማድረግ የመሪነትን ኃላፊነት ማጎልበትና ማኅበራዊ ተሳትፎ ማድረግ ናቸው፡፡

ብርሀን፡- የወንጌል ስርጭት ቡድናችን በተለምዶ ‹‹አክሽን ግሩፕ ›› ተብለው የሚጠሩት በምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

አቶ እንዳልካቸው፡- አሁን ሁለት ቡድኖች ሲኖሩን ሦስተኛውን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይዘታቸውን በተመለከተ በሳምንት አንድ ቀን የፀሎት ጊዜና የወንጌል ሥርጭት ጊዜ አላቸው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩ እነዚህ ቡድኖች ከቢሮው በፊት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ችግር ሌሎችም ወጣቶች ስብሰባ ባደረጉ ቁጥር የወጣት ለክርስቶስ ቢሮ ስም የመሰብሰባቸው ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቶች ስብሰባ ባደረጉ ቁጥር የወጣት ለክርስቶስ ቡድን ይባላል፡፡ እኛ ግን በትክክል የምናውቃቸውና የምንቆጣጠራቸውም በልደታ እና በባንቢስ ያሉት ሲሆን በሴንትራል ሸዋ አካባቢም አዲስ ለመክፈት ተዘጋጅተናል፡፡ እኛ የምንቆጣጠረው የሚያገለግሉት አገልጋዮች የወንጌላውያን አማኖች እንደሆኑ ጤናማ ትምህርት እንደሚያስተላልፉና አዳዲስ ነፍሳት ወደ የስብሰባዎቹ እየመጡ ነው ወይ? የሚሉትን ሐሳቦች ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያን ከሚጋበዙ ይልቅ እንዲህ አይነት ቦታ ቢጋበዙ ሚመርጡ ወጣቶቸች ስላሉ ውጤታማነቱን እየተመለከትን ነው፡፡ ሌላው በድሬዳዋ
የመሰረት ነውና 40 የሚያህሉ የወንጌል ስርጭት አገልጋዮች ያሉበት ቡድን ሲሆን በየሳምንቱ ከሚኖራቸው ስብሰባ በአንዱ ላይ 17 ሰዎች ጌታን እንደተቀበሉ አረጋግጠውልናል፡፡ በመዲናችን ካሉ የቡድን መሪዎች ጋር ሳምንታዊ የሆነ
ስብሰባ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ አንድ ለአንድ የወንጌል ሥርጭት ለሚለው አቋም ቡድኖቹ ውጤታማ ሆነው ነው ያገኘ ናቸው፡፡

ብርሀን፡- የበሰሉ ወጣት መሪዎች ለማፍራት ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው ያላችሁት?

አቶ እንዳልካቸው፡- መሪ ለማፍራት ዋነኛው መንገድ ሥልጠና ነው፡፡ በያዝነው ዓመት እንኳን ሁለት ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በድሬዳዋም አካሂደናል፡፡ ሌላው በወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናትና በተባባሪ አባላት በተሰጡ ሴሚናሮችም ላይ ተሳትፈናል፡፡ በዚህ ዓመትም ሰፋ ያሉ የሥልጠና መርሀ ግብሮችም አሉን፡፡

ብርሀን፡- በወንጌል ሥርጭት አገልግሎቶች ጌታን የሚቀበሉ ወጣቶች በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲያዙ ምንያህል ጥረት ታደርጋላችሁ?

አቶ እንዳልካቸው፡- እኛ የድኅነት (የመዳን) ትምህርት አናስተምርም፡፡ በሌላም በኩል ጌታን በተቀበለ በሳምንቱ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሄድም አናደፋፍርም ለአምስት ተከረታታይ ሳምንታት በዛው እንዲከታተል ከተደረገ በኋላ በመሪዎቹ ይመከርና ቤተክርስቲያን እንዲሄድ ይደረጋል፡፡

ብርሀን፡- የወጣቶች ማዕከል የማቋቋም ዕቅድ አላችሁ? ካላችሁስ ደግሞ ዳር ለማድረስ ምን ያህል እየተንቀሳቀሳችሁ ነው?

አቶ እንዳልካቸው፡- የወጣቶች ማዕከል የማቋቋም ዕቅዱ አለን፡፡ ማዕከሉ ሊያካትትልን ይችላል ብለን የምናስባቸው የወንጌል ስርጭት ስብሰባዎች፣የትምህርት ጊዜ ፣ የማማከር አገልግሎት ፣መፅሐፍት ቤትና የመዝናኛ ስፍራዎችን ነው፡፡ ባለንበት ዘመን የሥራ አጥነት ችግር ተንሰራፍቷል፡፡ ወጣቱም የሚቀጠርበት ቦታ ካላገኘ እንዲሁ ቁጭ ይላል እንጂ ሥራ የመፍጠር ባህልን አላዳበረም፡፡ ሥራ አጥነት እራሱ ብዙ መዘዝ ያስከትላል የቤተመጻሕፍት እንደልብ አለመገኘት፡፡ በተማሪዎችም ላይ ችግር ስለሚፈጥር ማዕከሉ በዚህ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እናምናለን፡፡እንግዲህ ዓላማችንን ወደ ፍፃሜ ለማድረስ አንዳንድ እርምጃዎች እየወሰድን እንገኛለንለ፡፡ ትልቁ ችግራችን ግን መሬት የማግኘቱ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከዓለም አቀፉ የወጣት ለክርስቶስ አካል ጉዳዩን አንስተን ተነጋግረንበታል፡፡ እነርሱም የራሳችሁ ቦታ ካገኛችሁ ብዙ ወጪ የማያስወጣ ቤት በነፃ መጥተው እንደሚሰሩልን ቃል ገብተውልናል፡፡ መንግስት ቦታ እንዲሰጠን ማመልከቻ ያስገባን ሲሆን ኪራይ ቤቶችም ቤቶቹን ይሸጣል እየተባለ ስለሆነ ለመግዛትም ሐሳቡ አለን፡፡ የፕሮጀክት ኮሚቴም አቋቁመን ገንዘብ የምናሰባስብበትን መንገድ እያሰብንበት እንገኛለን፡፡

ብርሀን፡- አብዛኛው ወጣት በዚህ ቢሮ ምን ያህል ይታመናል? ከማዕከሉ በፊትስ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅታችኋል?

አቶ እንዳልካቸው፡- አገልግሎታችን ታዋቂ እንደሆነ ይህንን አውቃለሁ፡፡ ዓላማችንን የበለጠ ለማወቅ የሚፈልጉና በአገልግሎታችን መሳተፍ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ደብዳቤ ይጽፉልናል፡፡ አብያተክርስቲያናትም ደጋግመው እንድናገለግላቸው እየጠየቁን ሲሆን ሥልጠናዎችንም አብረን በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡ ‹‹ሌላው ወጣት ለክርስቶስ›› በሚል ስያሜ የምናወጣው ጋዜጣ ሥራችንን በይፋ ታስተዋውቅልናለች፡፡ የመዘምራኑም ቡድን በራሱ፡፡ የማማከር አገልግሎት ስለተባለው ከማዕከሉ ምሥረታ በፊት አስበን ነበር ይሁንና ቦታው ሳይዘጋጅና ሰው ራሱ ሳይሰበሰብ አማካሪዎችን ማስተባበር አመቺ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ችለናል፡፡ ሁነኛ የሆኑ አማካሪዎች በተለያየ ቦታ ስላሉ እነርሱን በመጠቀም የራሳችንን አማካሪዎች እንዲያሰለጥኑልን ለማድረግ በዕቅድ ላይም እንገኛለን፡፡ ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን በመጀመሪያ ወጣቱን ማግኘት ነው የሚኖርብን ከዚያ በኋላ የማማከሩን አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች አይሆንም፡፡ ለዚህም የማዕከሉን መቋቋቀም አስፈላጊነት መመልከት ይቻላል፡፡ በመድረክ ወይንም በምስባክ ላይ ብቻ የማንጨርሳቸው ብዙ የምክር አገልግሎት የሚሹ ጉዳዮች ለመኖራቸው እርግጥ ነው፡፡

ብርሀን፡- አገልግሎት ጋብቻ፣ትምህርት ሥራና ሌሎችም የወጣቱን ዋነኛ ጥያቄዎች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዐውደ ጥናት አዘጋጅቶ የሚቀርቡትን ወረቀቶች አጣምሮ የማሰራጨት እቅድ አላችሁ?

አቶ እንዳልካቸው፡- ካሁን በፊት በምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ላይ በመንተራስ ሥልጠና ብቻ ነው የሠጠነው አንዳንድ ቤተክርስቲያናት ወጣቱን በተመለከተ ከአገልጋዮች ጋር ያለመግባባትና ሌላም ችግር እንዳለ ገልፀውልን መድረክ እንድናዘጋጅላቸው እየጠየቁን ነው፡፡ የሚቀርቡልን በርካታ ግብዣዎች በዚህ መልኩ እንድንራመድ አቅጣጫ እያስያዙን ሲሆን በጉዳዪም ላይ ከቦርዱ ጋር እየተማከርንበት ነው፡፡

ብርሀን፡- ከዚህ ቀደም ኮንፈረሶች ስታካሂዱ የቦታ ጥበት አጋጥሟችሁ ነበር አሁን ችግሩን ለመቅረፍ ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?

አቶ እንዳልካቸው፡- በዚህ ዓመት ኳስ ሜዳውን የመጠቀም እቅድ አለን፡፡ ኮንፈረንሶቻችንን የምናካሂደው ከትምህርት ጊዜ ውጭ በክረምት ስለሆነ የዝናቡ ሁኔታ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በበጋው ወራት የእረፍቱ ጊዜ አመቺ ከሆነ ስቴዲየሙን ለመጠቀም አቅደናል፡፡ የኤግዚቢሽን ማዕከልን አስበን ነበር ዋጋው ስለተወደደብን ግን ትተነዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ቦታዎችን የምንጠቀምባቸው ዋነኛ ምክንያቶች የወንጌልን ዘር ለመዝራት ሰው እንደሚያበራክትልን በማመን ነው ብዙዎች አስቀድመው ቤተክርስቲያን ከሚሄዱ ይልቅ እነዚህ ቦታዎች ይመርጣሉ፡፡ የወጣቶች ሳምንት አዘጋጅተን የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት አቅደናል፡፡

ብርሀን፡- ከሌሎች ዓለም አቀፍ ቢሮዎች ጋር ልምድ ትለዋወጣላችሁ?

አቶ እንዳልካቸው፡- በየሦስት ዓመቱ የሚደረግ ዓለም አቀፍ የልምድ ልውውጥ ስብሰባ አለ፡፡ በአፍሪካ ደግሞ አመታዊ ስብሰባዎች ይደረጋሉ በነዚህም ስብሰባዎች ናሙና የሆኑ ፕሮጀክቶች ይቀርባሉ፡፡ ሌላው ትምህርት ይወስዳል፡፡ የአካባቢው ኃላፊ በመጋቢት ወር ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመጡ ብዙ ነገር ለመማማር ተዘጋጅተናል፡፡ከካቶሊክና ከኦርቶዶክስ ወጣት መሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ለጠየኩት ጥያቄ ሲመልሱ ኮንፍረንሶች በምናዘጋጅበት ጊዜ ትኬቶች እንደሚልኩላቸው የገለፁ ሲሆን ካቶሊኮች በዲአፍሪካ አዳራሻ ባዘጋጁት ስብሰባ መክፈቻ ላይ ተጋብዘው እንደተገኙም ገልጸውልኛል፡፡ በመጨረሻም ዋነኛ ዓላማቸው ከዓለቱ ጋር የተጣበቀን መልዕክት ጊዜውን ባገናዘበ መንገድ ማሰራጨት እንደሆነ ከገለፁ በኋላ የመፅሔቱ ታዳሚዎችም ሆኑ ሌሎች ለአላማቸው ዳር መድረስ ድጋፋቸውንና ፀሎታቸውን እንዲያስተባብሩ ጠይቀዋል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox