ወላጆች እና ተወላጆች – ብርሃን መፅሔት 1991 ቁጥር 32

ከጌታቸው በለጠ :

የየሀገሩን መንግስታት ና ወላጆች እያነጋገሩ ካሉ ዋንኛ አጀዳዎች አንዱ የወጣቶች ጉዳይ እንደሆነ የመገናኛ ብዙሃን በዕየለቱ ይነግሩናል የወጣቱን ጥፋትም እየዘረዘሩ ያስደነግጡታል ሥልጡን ነን በሚሉት የምዕራብ አገሮች ወይንም ሥልጣኔን እየደረስንበት ነን እያሉ በሚጣደፉ ታዳጊ አገሮችም ወጣቶችንም በተመለከተ የሚወራውና የሚያስተውለውንና የሚጻፈው ሀተታ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ‹‹ጆሮን ጭው›› ማድረግ ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ዛሬ ዛሬ በወጣቶች ጥፋት ላይ ጣቱን የማይቀስር አባል መኖሩን ያጠራጥራል በቀዳሚነት ወላጆች የልጆቻቸውን ነገር ከአቅማችን በላይ ሆኗል በማለት ስሞታ ከማሰማት አልፈው ተርፈው በአውራጎዳናዎቹ ላይ እየተሰለፉ ‹‹መንግስት ሆይ ልጆቻችንን አንድ በልልን ››ማለት ከጀመሩ ሰነባብቷል አቤቱታቸው በመንግስት አጣዳፊ ምላሽ እንደጣ የተረዱት ወላጆች የልጆቻቸውን ልጅነት ክደው የአብራካቸውን ክፋይ መብት ገፈው ከቤት ያባረሩ ለጠባይ ማረሚያ ተቋማት እጃቸውን አንጠልጥለው የሰጡ ለፖሊስ አመልክተው በካቴ ያስጠፈሩ ወላጆች ዜና ከመደመጥ አልፎ መሰልቸትን አትርፏል::

መንግስትም ‹‹የወጣቶችን ጉዳይ ራስ ምታታ ሆኖብኛል›› በማለት በየአደባባዩ በፖሊስ ቆመጥ ሲያስደበድባቸው እንደሚውል የሬድዮና የቴሌቭዥን ሞገዱ ውቅያኖስ እያቋረጠ ቤታችን ድረስ በመምጣት አሰቃቂውን የዓለማችንን ዜና በግድ እያስደመጠንና እያሳየን ነው ‹‹ፓለቲካዬን ተቃውሙ አድማ ወጡብኝ ካቢኔዬን ተዳፈሩ ሸንጎዬን አንቋሸሹ……›› በማለት መንግስታት ከወጣቶቻቸው ጋር የጎሪጥ እየተያዩ ይገኛሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም በወጣቶች ጉዳዩ ጤና አጣን እያሉ ሮሮ ማስደመጥ ከጀመሩ ሰነባብተዋል የእነርሱ ምክንያት ደግሞ እንዲህ የሚል ነው ‹‹የሀሰት ትምህርት ጉባዔያችን መሃል ረጩብን አዳዲስ ልምምዱች አስርገው አስገቡብን በአመራር ዘይቤአችን ላይ አቃቂር አበዙብን የሕዝቡን የአምልኮ ባህል አበላሹብን የተሃድሶ ድፍረት ፈጸሙ ብን….›› ምን ይባላል የማይባል አለ፡፡ ስለዚህ የወጣቱ ዕድል ፈንታ የባህር ላይ ኩበት ከሆነ ውሎ አድሯል የወላጆቻችንም የመንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ፊት የጠቆረበት የዘመናችን ወጣት መሸሻ አድርጎ የመረጣቸው ማጽናኛዎች በእጅጉ የሚሰቀጥጡ ድርጊቶች ናቸው የፈለገውን ምርጫ ይወስዳል የወደደውን ይከተላል ይገድላል ይገዳደላል በአደንዛዥ ዕፅዋት ህሊናውን ገድሎ የቅዠት ዓለም ውስጥ ይኖራል በቁማርና በማጭበርበር ተሰማርቶ ራሰነ ይኖራል ሌላውም ያጠፋል በሕክምና አልባ የዝሙት ደዌዎች እየተለከፈ ለረሱም ለሌላውም የሞት ፅዋ ያቀብላል እኔ ከሞትኩ…….እንዳለችው እንሰሳ ብጤ ያልተቀበለችውን ዓለም ሊበቀል ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ የዘመናችን ወጣት መሸሻ ወዴትናወደማን ይሁን? ማን አለሁ ይበለው እንደዚያ ርህሩህ ሳምራዊ ሳይጠየፈውና ሳይፈራው ተጠግቶ ማን ይቀፈው ማን ያስታመው ማን ያክመው ለውይይት የሚጋብዙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የውይይት መነሻ ሃሣባችንን አጥብበን በሀገራችን ጉዳዮችና በቤተክርስቲያን ኃላፊነት ላይ ማተኮር አግባብ ስለሆነ እንሆ የወጣቶቻችን የሀገራችንና የቤተክርስቲያናችን ገበና ይህን ይመስላል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ከ60-65% የሚሆነው ወጣት እንደሆነ የሕዝብ ቆጠራው ስታስቲክስ ውጤትና የልዩ ልዩ ተቋማት ጥናቶች ያስረግጡልናል በቅርቡ በዚህ ጉዳይ የአብዛኛዎቹን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በር በማንኳኳት የሀገራችን ወጣት የሕይወት ገፅታ ምን ይመስላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማፈላለግ የሞከሩ አንድ ወዳጄ ያሰባሰቡት ግርድፍ ጥናታዊ መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ከ18-69 ዓመት ክልል ውስጥ ከሚገኘው ሕዝባችን መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በዝሙት ደዌ የተለከፉት……20%
የመጠጥ ምርኮኛ የሆኑት……40 %
ሲጋራ የሚያጤሱ………….30 %
በጫት ሱስ የተቁራኙ………40%
በአደንዛዥ ዕፅ የሚናውዙ…..2%
በሌብነት የሚተዳደሩ……..5%
የለሊት ክበባት ደንበኞች……1%
የቃልቻ አምላኪያን……30%
ፈጣሪ የለሾች………10%

እነዚህ አሃዞች ምን ያህል አስደንጋጭ አሳዛኝና ህሊናን የሚያቆስሉ እንደሆኑ አንባቢው በስሜቱ ሊመዝናቸው ይችላል ከላይ ለተዘረዘሩት ማሕበራዊ ‹‹እርግማኖች›› እንደምክኒያት የሚሰጡት ሳይንሳዊ ትንታኔዎች (ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማኀበራዊ ግንኙነቱ ወዘተ…) እንደተከበሩ ሆነው የሥነቃል ውርሳችን ያደረሰብን ጉዳት በወንጀለኝነት ያስጠይቀዋል ሥነ ቃል የምንለው የዕውቀት ዘርፍ ከቃል ወደ ቃል በተርታ ተረት በምሳሌና በእንቆቅልሽ በሰባባሎች በዘይቤያዊና በፈሊጣዊ አነጋገሮች ወዘተ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል እየተላለፈልን የመጣ ቅርስ ነው ይህ ቅርስ ሙሉ በሙሉ መጥፎ ነው ለማለት በፍጹም ባያስደፍርም ጉዳት እንዳለው ግን መግለጽ አያዳግትም የባህል ደግ እንዳለሁሉ ክፉም ስላለ በተለይም ከዚህ ርዕስ ጉዳይ ጋር የተገናኘውና የወላጆችና የልጆችን አብዛኛው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ከሚገልጡት ምሳሌያዊ ግንኙነት ከሚገልጡት ምሳሌያዊ አነጋገሮች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል፡፡

-ልጁን በራብ የእንጀራ ልጁን በጥጋብ
-ልጅ ለሣቀለት ውሻ ለሮጠለት
-ልጅ ቢያስብ ምሳውንአዝማሪ ቢያስብ ጠላውን
-ልጅ ታጉል እህል ከጉውር
-ልጅ አባቱን ገደለው ቢለው የኔልጅ እንዳይሰማ አለው
-ልጅ ከዋለበት ሽማግሌ አይውልም
-ልጅ ያለ ልጅ አከለ
-ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም
-ልጅ ይወለዳል ከቦዝ ላም ይገዛል ከወንዝ
-ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ
-ልጅህንና አትክልትህን ተጠባበቅ ጎረቤትክን
-ልጅና ጥሬ አይተጣጡም
-ልጅና ጦጣ ውሃ ይጠጣ
-ልጅን በጡት እህልን በጥምቀት
-የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ…..ወዘተ

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሃገርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች በአብዛኛው ለልጅ የተሰጠውን አነስተኛ ሥፍራ የሚጠቁሙ ናቸው ልጅ አያውቅም ልጅ አይበቃም ልጅ አይታመንም ከልጅ ቁምነገር አይገኝም ወዘተ…. የሚሉትን እነዚህን መሰል አባባሎች እየተጋቱ ያደጉት ወጣቶቻችን ውጤት እንሆ ዛሬ የሆኑትን ሊሆኑ አስችሏቸዋል ወላጆቻቸውም ‹‹የልጅ ነገር እየተባሉ ስላደጉ እነርሱም በተራቸው ልጆቻቸውን ‹‹የልጅ ነገር›› እያሉ ቢያዋክቡ አይደንቅም የሀገር መሪዎችና የቤተክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ አንጋፋ አገልጋዮች ያው የማኀበረሰቡ አካል ናቸውና እነርሱ እንዳደጉት የልጆቻቸውን አፍ እየመቱ እንምራ እናስተዳደር ቢሉ እኛ እንዳደግን እናንተም እደጉ ማለታቸውን እንደሆነ ልንረዳ ይገባል ግን እንደትናንቱ የዛሬም ሕይወት አንድ ነው ወይ ትናት ልጆችን የበታችነት ባጸደቀ ኀብረተሰብ ውስጥ አድገናልና ልጆቻችንም እንደዚያው ማደግ አላባቸው ወይ እስከመቼስ ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም እየተባለ ሲተረት ይኖራል እስከመቼስ የልጅ ነግረ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ እየተባለ ሲወገዝ ይኖራል ሰፊ ርዕስ ሁሉንም የሚነካካ ቢሆንም ርዕስ ጉዳዩን በማጥበብ ሌላውን ለሌላ ቀጠሮ አቆይተን የውይይቱን አቅጣቻ ወደ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና ወደ ወንጌል አማኙ ወላጅ ማመልከቱ መልካም እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

‹‹ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው ከአደገ በኋላ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም (ምሳ.22፤8) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለልጅ አስተዳደግ የጠበቀ መርህ ነው ልጅ በትችት ካደገ ተቺ በዘለፋ ካደገ ዘላፊ በፍቅር ካደገ የፍቅር ሰው እውነት እየሰማ ካደገ የእውነት ሰው ሰላም እያደመጠ ካደገ የሰላም ሰው ዕርቅን እያስተዋለ ካደገ ታራቂና አስታራቂ ጉብዝናን እያስተዋለ ካደገ ታታሪ ጸሎትና የእውነት ቃል እየተማረ ካደገ የጸሎትን ሰውና የእውነትን አስተማሪ በርታ እየተባለ ካደገ ጠንካራና አበረታች ሆኖ ያድጋል እናም ዛሬ ወጣቶቻችን ልጆቻችን በቤተሰባቸው ውስጥና በቤተክርስቲያን ቤቱ ምን ይመስላል ከልጆቹጋር ያለውን ህብረትስ ቢቻል በዕለቱ ባይሆንም በየሣምነቱ ካልተሳካ በየወሩ ምን ያህል ቀን ለልጆቹ ጊዜ ሰጥቶ አብሮ ይጸልያል አብሮ ይዘምራል አብሮ ይማማራል አብሮይወያያል እኔም የሐዋርያው ጳውሎስን ጥቅስ ታክኬ እንዲህ እላለሁ ‹‹ስለቤተሰቦቹ(ልጆቹ) የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው›› (1ጢሞ.5፡8) ወደ ቤተክርስቲያ መሪዎችም ዓይናችንን ስናቀና የምናስተውለው ነገር በእጅጉ ልብን ዓይንንም የሚያስለቅስ ነው ወጣቶችን የሸሹ በወጣቶቻቸው ላይ አምስት ጣቶችቻቸውን በመጠቆም እንደ በረከት ስንሆን እንደ‹‹እርግማን›› እየተመለከቷቸው ነጋ ጠባ የወጣቶችን ጉዳይ የሽማግሌዎች ጉባኤ የመወያያ አጀንዳ የሆነባቸው ቤተክርስቲያናት ቁጥር ቀላል እንዳይደለ እንገምታለሁ ቢያንስ እኔ ስለማመልክበት ቤተ ክርስቲያን በድፍረት መናገር የምችልባቸው ብዙ ጎዳዮች መኖራቸውን አውቃለሁ፡፡

‹‹ክፉ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንደተባለው መሪዎች ወጣቶችን አስበርግገው ሲያሸሷቸው ማን ይጠየቅ ወጣቶቹስ በርግገው ጥፋት ሲፈጽሙ እንዴት ይመክሩ ውይይታችን ያዳብረዋል ፡፡ ለመሆኑ ቤተክርስቲያን ለወጣቶቿ መመገብ ያለባት መንፈሳዊውን ምግብ ብቻ ይሆንን ስለአካዳሚክ ትምህርታቸው ለሀገርና ለወገን ማበርከት ስለሚገባቸው ምልካም ተግባር ስለሥነ-ምግባርና አብሮ መኖር ስለ ዜግነት ግዴታና መብት ወጣቶቻችን በግልጽ ሊማሩ አይገባ ምን የቤተ ክርስቲያ ድርሻ መንፈሳዊውን ሰው ለሰማያዊ መንግስት ማብቃት ብቻ ነው ወይንስ የበቁ ዜጎችን ለህዝብና ለመንግስት አደራ ጭምር ማፍራት ነው ዛሬ ከ80% በላይ ምዕመናን ወጣቶች ለሆኑባቸው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ተግዳሮት ቀላል እንዳይደለ ሊታሰብ ይገባዋል፡፡ ቢያንስ ቤተክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው ያሉትን ወጣቶቻችንን ለዓለም ጨውና ብርሃን እንዲሆኑ ወላጆችና ቤተክርስቲያናት ጠንክረው ቢሠሩ ለዛ ጣዕሙ ለጠፋበት ዓላማችን ሀገራችን መፍትሄና ተሰፋ መሆን እንደሚቻል ጸሐፊው አጥብቆ ያምናል፡፡ የወጣቶችን ልብ ክፍት ነው ቀድሞ ገብቶ ልባቸውን የሚዘጋውን ኃይል ለማስወጣትም ቀላል አይሆንም ሌላ ሃይል የወጣቶቻችን ልብና ስሜት ከመግዛቱ በፊት ወላጆች የቤት ውስጥ አደራውን ይወጡ ቤተክርስቲያናትም የአደባባዩን ድርሻ ይውሰዱ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት እናስተምራቸው እንቅረባቸው እናወያያቸው እንገስጻቸው አናርቃቸው አይዙዋችሁ እንበላቸው ወላጅ ለራቀው ወጣት የወላጅ ያለህ መንገግስት ፊቱን ላጠቆረበት ወጣት የመንግስት ያለህ ቤተክርስቲያን ላልተቀበለችው ወጣት ደግሞ የመሪ ያለህ እየተባባልን ልንጠራራ ልንመካከር አቅጣጫና መፍትሄዎችን ልንቀይስ ይገባል፡፡ ግርድፉ ቅኝት ለውይይት ቢያበቅ ብዬ ብእሬን በአጠቃላይ ግርድፍ ቅኝት አንድ አሰኝቻለሁ ሌሎች ሁለት ሦስት የሚሉ ተወያችናና አወያዮችን ደግሞ ብርሃን ተቀብላ እንደምታስተናግድ አምናለሁ ይሄው ነው ለወላጅና ለተወላጁ እግዚአብሔር ይሁንልን የወጣቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚለው ሁሉ ትውልዱን ለማዳን የሚያስችለውን ድርሻ ለመውጣት ፅኑ ፍቅርና የርህራሄ ልብ ለመልካም ሥራ ረበረታ እጅ ይስጥልን፡፡

ብርሃን መፅሔት
1991 ቁጥር 32

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox