አለቃ ታዬ እስራትና ግዞት ያልሰበረው ቅስም

ብርሃን መፅሔት ቁጥር 36 :

አዛውነቱ ገ/ማርያም ኪ/ማርያም ዳዊት ከመድገም ያለፈ እውቀት አልነበራቸውም ከጥቁር አፈር ታግለው የመሬትን እንብርት በመገልበጥ ሙያ ግን ተክነውበታል ያብራካቸው ክፋይ ታዬ ሞፈር ከቀንበር ማቀናጀት የማለዳ እጣክፍሉ አልነበርም ብራና ከመቃ ብዕር ከወረቀት አንጥቦ ሆሄያትን የሚያበራይ ስሉጥ የቀለም ቀንድ እንጂ፡፡
እምር ታህል ልጅ እያለ ወደ ቤተክህነት ትምህርት የተላከው ታዬ ስምንት ዓመት ሲሞላው ንባብና ጽሕፈትን አቀላጥፎ እንደቻለ ይነገርለታል የተወለደበትን ዘመን አስመልክቶ በእድሜ ከገፋ በኋላ ከኪሱ በማትለይ አንድ የግል ማስታወሻው ላይ የተገኘው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹የአለቃ ታዬ ልደት 1853 ዓ.ም ወንጌላዊ ሉቃስ 20 ወ 1 ለኅዳር ነው፡፡ይህም ዐጼ ቴዎድሮስ በነገሱ በ7ኛው ዓመት ነው ያጼ ቴዎድሮስ መንግስት 15 ዓመት ነው፡፡ ካጼ ቴዎድሮስ መንግስር 8 ዓመት አመጣለሁ በአውሮፓ ቁጥር ግን 1861 ተወለድኩ በኖቬምበር ወር 30ኛው ቀን፡፡›› ኤሬክስ የተባለው የውጭ ዜጋ ይህንኑ የታዬን የግል ማስታወሻ ካነበበ በኋላ በአውሮፓውያን የዘመን ቀመር ላይ መጠነኛ ማስተካከያ አስቀምጧል እንደታዬ አባባል ይለናል ኤሬክሰን ‹‹ተወለድኩ›› የሚለን በኢትዮጵያ አቆጣጠር ኀዳር 21 1953 ከሆነ የዘመኑ ስሌት ወደ አውሮፓውያን ቀመር ሲመነዘር ኖቬምበር 30 1960 እንጂ ኖቬንበር 30 1961 አይደለም ነው የሚለን፡እንደታሪክ ጸሐፊው ጎስታቭ አባባል ከጣና ሐይቅ በስተ ምስራቅ በምትገኘውና ‹‹ይፋግ›› በተሰኘችው የገበያ ማዕከል የተወለደው ታዬ እድሜው አስራ አምስት ዓመት ሲሞላው የዳኸባት መንደር በወረርሽኝ መቅሰፍት ተመታች አስቀድሞ መንደሪቱን ለቆ ከሄደው ወላጅ አባቱ በቀር ያማጠችውን እናቱን ጨምሮ የቀሩትን ዘመዶቹ በበሽታው ረገፉ የሁለት ወላጆቹን ባጣው በዚህ ሕፃን ልብ ውስጥ ሰቀቀን ነገሰ ብቸኝነቱም አባቱን ፍለጋ አገር ለቆ እንዲሄድ ገፈተረው፡፡ የታዬን የህይወት ታሪክ የፃፈው ኃይሉ ከበደ ለሕትመት ባልበቃ ሥራው ታዬ ለስደት ከወጣበት ሁኔታ እንዲህ ይተርካል፣

‹‹ አባታቸው ወደሚገኙበት ወደ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ለመሄድ ሞክረው ሳይሳካላቸው ስለቀረ የናታቸው ወንድም የሚሆኑት አጎታቸው ትግራይ ይኖሩ ስለነበር ጉዞአቸውን ወደዚያው አመሩ ትግራይም እንደደረሱ አጎታቸውን ስለአጧቸው ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ አቅደው ምጽዋ ደረሱ እግረምንገዳቸውን የስዊድን ሚስዩን ትምህርት ቤት እንዳረፉ ከዚያው መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቀጠሉ፡፡››
ከዚህ ላይ የታሪክ ክፍተት እንዳይኖር የኃይሉን ፍሰት እንገታና ታሪክ ጸሐፊውን ጉስታን በእዝል(^) እንሸንቁረው ‹‹. . . የአሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ታዬ ምጽዋ ከወረደ በኋላ አጎቱ ባህር ቀዝፈው ወደ ሕንድ መዝለቃቸውን ሰማ በዚህም ምክኒያት አሳቡን ቀይሮ እምኩ ወደሚገኘው የወንዶች ትምህርት ቤት ለመግባት ወሰነ፡፡ ከተቀሩት ልጆች አንጻር ሲታይ በእድሜ ጠና ማለቱን የገመተው ሎንደን በመጀመርያ ታዬን ለመቀበል ቢያንገራግርም ጥቂት ወራቶች ካፉ በኋላ ግን እንዲማር ፈቀደለት፡፡››

በትምህርት ቤት በቆየባቸው አመታቶች ስል አእምሮ እንዳለው አስመሰከረ፡፡ እንደ ዊንክቨስት እና ኤሚሊ ሎንደን ( መምህራኑ) ዕይታ፣ ታዬ በባህላዊ ትውፊቶች ዙሪያ እንደመመሰጡ ከምዕራባውየን ትምህርት ይልቅ ለምስራቁ ቅድሚያ ሲሰጥ ታይቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልዩ ዝንባሌ አለው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያንን አስተምህሮ ለማጥናን ሰፊ ጊዜ ይሰጣል አብዛኛውን ጊዜ እስከ ሌሊቱ አጋማሽ ድረስ ከግእዝ መጽሐፍት እያጣቀሰ ይመራመራል በማለት መስክረውለታል፡፡
በኖቬምበር 12 1881 ታዬ የቤተል መኀበረ ምዕመን አባል በመሆን ከጉባዬው ተቀላቀለ ኤሚሊሎዳል ከመሞቱ አስቀድሞ ስለሰራቸው የጽሁፍ ሥራዎች ባወሳችበት የጽሁፍ ማስታወሻ ላይ የሎንደል ተጠቃሽ ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ መሆኑን ጠቅሳ ይህ የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ታዬ እመኩሉ ተማሪ በነበረበት ወቅት የተከወነ ቢሆንም ጽሑፍን በመገልበጥና ቋንቋውን በማቅናት በኩል ታዬ ጥሩ እገዛ እንዳደረገ ታወሳለች በተለይም በዩሐንስ ወንጌል ላይ የተሰራው ሐተታ ሎንዳል ባረፈበት ወቅት አብዛኛው ክፍሉ ተቃጥሎ ያለቀ ቢሆንም መልሶ በመከለስና ለሕትመት አመቻችቶ በማቅረብ በኩል የእኔ /ኤሚሊ/ የታዬና የአናሲሞስ እጅ አለበት ነው የምትለን፡፡ በተከታዩ ዓመት ማለትም በኖቬንበር 1882 ታዬ ቅኔ ለመቀኘት ፊቱን ወደ ቤገምድር መለሰ፡፡ በሚገናኙበት የታሪክ ፈለግ ላይ በማረፋችን በኃይሉ የታሪክ መስመር ጥቂት እናዝግም ‹‹. . . ምንኩሉ ከተባለ ሚስዮን ትምህርት ቤት ለብዙ ዓመት የወንጌልን ቃል ሲመራመሩ ቆይተው እንደገና ወደ ትውልድ ሃገራቸው ተመለሱና የግእዝ ቅኔ ትምህርት ቤት ገቡ በዚያ የግዕዝን ቋንቋ ጠንቅቀው እንዳወቁ በ1877 ወደ ምጽዋ ተመልሰው በመምህርነት ሙያ እስከ 1990ዓ.ም አገለገሉ በዚያዘመን የድርሰት ሥራ እንደጀመሩ ይታመናል ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው›› የተባለውን መጽሐፍም በዚሁ ጊዜ ጻፉት፡፡ ይህንኑ ሁኔታ አስመልክቶ ጎስታቭ ሲናገር ‹‹ታዬ ሌጣውን ሳይሆን ያገኘውን መንፈሳዊ መረዳት ጭምር ይዞ ነበር ወደ መንደሩ የተመለሰው መጽሐፍቅዱሳዊ እውቀቱን ለሌሎች ሊያጋራ ቢሻም ጆሮአቸውን አልሰጡትም በመሆኑም የቅኔ ትምህርቱን በሙሉ ቀልቡ መከታታል ቀጠለ ምርምሩንም በተለያዩና ዕውቅና ባላቸው አድባራት ገዳማት ካጠናቀቀ በኋላ፤‹‹አለቃ›› የተሰኘውን ከፍተኛ ማዕረግ ተቀዳጀ፡፡ ከዚያም በዲሴምበር 1883 ወደ እምኩሉ ተመልሶ በመምሕርነት በአስተርጓሚ በወንጌል ሰባኪነት አግልግሏል፡፡ በ1890 እንደገና ወደ ትውልድ መንደሩ ተመለሰ በዚያም ትዳር መሥርቶ የወንጌልን ስብከቱን ቀጠለ፡፡ በሙያውም ተወዳጅነት በማትረፉ በዘመኑ ቤገምድርን በከፊል ይገዙ የነበሩት ራስ መንገሻ አትክም በወዳጅነት አቀረቡት ከጥቂት ጊዜ በኋላም የታዬን ሊቅነት በመገንዘብ አሽከራቸውን ባልደረባ ሰጥተው 1891 ዓ.ም ወደ አፄ ምኒልክ ላኩት በወቅቱ ራስ ምንገሻ ዮሐንስ ሽፍትነት በመግባታቸው ሳቢያ በራስ መኮንን የሚመራ ጦር ወደ ትግሬ ተልኮ ነበርና ንጉሱ አፄ ምኒልክ የሠራዊቱን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል ደነባ ወሎ ላይ አርፈው እያለ አለቃ ታዬ ከንጉሱ ቀርበው ተዋወቁ እምኩሉ ሳሉም አሳትመውት የነበረውንና ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው›› የተሰኘውን መጽሐፋቸውን ለጃንሆይ አበረከቱ ንጉሱም ሥራውን አይተው በመደሰት ሊቁን ካበረታቱ በኋላ ከትውልድ ቦታቸው እንዲቆዩ አዘዟቸው፡፡

ከፊል ትምሕርታቸውን ከውጪ አገር ዜጎች ዘንድ በመቅሰማቸው ሰበብ አንዳንድ የቤተ ክሕነት ሰዎች በአለቃ ታዬ ላይ ተቃውሞ ያነሱባቸውና ያስነስባቸው ስለነበር ይህንኑ ጉዳይ ለጃንሆይ ምኒልክ አቅርበው የሚከተለውን ደብዳቤ ተቀበሉ፡፡
‹‹ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም የሚባል ሰው ምጽዋ የነበረ ሃይማኖቱን እኛ መርምረነዋልና ማንም አንዳች አይበለው በሃይማኖት ነገር፡፡ በኅዳር 6 ቀን 1891 ዓ.ም በወረኢሉ ከተማ ተጻፈ፡ቤጌምድር ተመልሰው ሥራቸውን ቀጠሉ አፄ ምኒልክ ከወሎ ተነስተው አዲስ አበባ እንደደረሱ ታዬም ወደዚያው ወርደው ከንጉሱ ጋር በመገናኘት ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴን ባልደረባነት ተቀበሉ በጊዜው አንዳንድ ሰዎች ‹‹የታዬን ሀይማኖት የፈረንጅ ነው ጃንሆይ ይህን ሳያውቁ ነው ማኀተም የሰጡት›› በማለት ስላሶሩ አቡነ ማቴዎስና ጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ ተቀናቃኝ ሆነው ተነሱባቸው ይህም ሁኔታ በጸሐፊው ገ/ሥላሴ በኩል ወደ አጼ ምኒልክ የመግባት እድላቸውን አክሰመው፡፡ እንደሚባለው አቡነ ማቴዎስ ጉባዔ ከተው አለቃ ታዬን ካስጠሩ በኋላ ‹‹አንተ አህያ ሃይማኖትሕ ምንድነው?›› በማለት ስለጠየቋቸው ጥያቄ አለቃ ‹‹እኛን አህያ የሚያሰኝ እናንተን መሾማችን ነው፡፡›› ሲሉ እንደመለሱላቸው ይነገራል ነገሩ እየከረረ በመምጣቱና በአለቃ ላይም የተፈጸመው በደል ጃንሆይ ዘንድ በመድረሱ ንጉስ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴን በመገሰጽ አቡኑም በማይገባ ሁኔታ አለቃን በማንገላታታቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ነግ በኋላ ታዬ የወንጌልን ሥራ ከማስተማር ጎን ለጎን የጽሁፍ ሥሰራቸውን ቀጠሉ ይህንንም በትጋት በማከናወን ላይ ሳሉ ከንጉሱ ዘንድ እንዲህ የሚል የማዘዣ ደብዳቤ ደረሳቸው፤ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘምነገደ ዩሁዳ ዳግማዊ ምኒሊክ ሥዩመ እግአብሔር ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ይድረስ ለአለቃ ታዬ እንዴት ሰንብተሃል እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህናነኝ ከጀርመን መንግስት ተልከው የመጡ ሰዎች በምጽዋ በኩል ወደሃገራቸው ለመሄድ በጎጃም በኩል ወጥተዋል ነግር ግን ከኢትዮጵያ የሄደ በአገራችን ብዙ የጥንት መጽሐፍ አለ ያንን የሚያውቅ ብልህ ሰው ይሂድና እንዲያይ ይሁን ብለውኛል አንተ የዚያን አገር ባህል ለምደኸዋልና እናንተ ዘንድ በደረሱ ጊዜ አንተም ከነሱ ጋር አብረህ እንድትሄድ ይሁን›› መጋቢት 9 ቀን 1897 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ፡፡
ይህን ጥሪ አስመልክቶ ክሪስ ፕሩቲ Empress Taytu and Menilek” በሚል ሥራው ‹‹ከጀርመኖች ዘንድ የመጣውንና በበርሊን የኦሬንታል (ምስራቃዊ) ጥናት ተቋም ውስጥ ባለሙያ የማሰማራቱን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ሊያሟላ የሚችል ከታዬ የላቀ ስመጥር የግእዝ ምሁር በምኒሊክ አእምሮ ውስጥ አልነበረም ያም በመሆኑ ለዚህ ሃላፊነት አጭተውታል›› በማት ጽፎአል፡፡ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወለደ ሥላሴ ‹‹የሕይወት ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው ይህንኑ ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል ‹‹የጀርመን መንግስት ግእዝ ቋንቋ የሚያስተምር አንድ ሊቅ ይሰጠኝ ብሎ አፄ ምኒልክን በለመነ ጊዜ አለቃ ታዬን መርጠው ሰደዱዋቸው በጀርመን መንግስት ሦስት ዓመት ሙሉ ግእዝ ቋንቋ አስተምረው ኒሻን ተሸልመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አፄ ምኒልክም ኒሻን ሸልመው ያባታቸውን አገር ሰጥተው ወደ ቤገምድር ሰደዱዋቸው፡፡››

ጉዞ ወደ ነምሳ (ጀርመን) ተጀመረ ታዬወደ አውሮፓ ባደረጉት መዋብ አያሌ ከተሞችን ቃኝተው አልፈዋል ለዚያም የጉዞ ማስታወሻቸው ሊጠቀሱ ይችላ ጥቂቱን ቆንጥረንለታል፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 22/1897 ‹‹በዚህ ቀን ሌሊቱን ስንሔድ አድረን ማለዳ ሲቂሊያ በ6 ሰዓት ደረስን ስንሄድ ውለን ማታ በ7 ሰዓት ኒያፖል ገብተን አደርን ሲቅሊያ የኢጣሊያን ክፍል ናት እርሱዋም ቃሮዳን የምታህል ታላቅ ደሴት ናት ከተሞቹዋም በባሕር ዳር ለዳር ተሰርተው እጅግ የሚያምሩ ናቸው፡፡ ሊፖልም በባህርዳር ዳር የተሰራ የጥንት የጣሊያን ነገስታት ከተማ ነው፡፡ ዛሬ ግን ራሱ ከተማው ሮም ነው፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 20/1697 ‹‹ በዚህ ቀን በማርሴል ዋልን ባቡሪቱ ዕቃ ስታወርድ ዕቃ ስትቀበል ዋለች እኔና ዮሴፍ ሱማሊ በ8ሰዓት ከባቡር ወጥተን በሠረገላ ከተማ ለከተማ ዕኩል ሰዓት ሄደን ወርደን በእግራችን ደግሞ እየዞርን ብዙ ነገር አየን በዚያም እጅግ ሐፍረት የሌላቸው ደፋሮች ጋለሞቶች አየን በ5ሰዓት ወደ ማታ ከባቡራችን ገብተን አደርን፡፡ አለቃ ጀርመን ዘለቁ እዚያም በቆዩበት ዘመን ከጃንሆይ ምኒልክ ጋር በመጻጻፍ መፈጸም የሚገባቸውን ሁሉ በትጋት ይከውኑ ጀመር በግእዝ የተጻፉ መጻሕፍት ከመመርመርና ከመሰብሰብ ባለፈ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ማስተማር ቀጠሉ፡፡ በዚያም በከራረሙበት ዘመን እአንዳንድ ሁኔታዎች ከየአቅጣጫው ከቃኙና ካስተዋሉ በኋላ ጳጉኔ 3 ቀን 1898 ዓ፣ም ለአፄ ምኒሊክ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉ፣
‹‹. . እኔ ያስተማርኳቸው አማርኛና ግዕዝ ያነባሉ ይጽፋሉ ደህና ሰዎች ናቸው የጃንሆ መልእክተኛ ብለው አክብረው አፍቅረው ይዘውኛል ከአገር ናፍቆት በቀር የጎደለብኝ ነገር የለም ለጥበባቸው ፍጻሜ የለውም የየዕለቱ አዲስ ነገር እሰማለሁ ጃንሆይ ከአገሮት ልጆች ወደ አውሮፓ ሰደው ብክሃት ያስተምሩ መልካም በሆነ የያጃንና የሞሮኮ መንግስት ቅንዓት እንደሳት በላኝ ምንኮ አደርጋለሁ አዝኜ ወደመቃብር እወርዳለሁ የጃንሆይ ብር እንዲሰለጥን የፊተኛውንብርና አሞሌ ያጥፉ፡፡. . ››
በማከታተከልም ግንቦት 1899 ዓም የውስጣቸውን ብሶትና የአገራቸውን ኋላ ቀርነት የሚያጣቁምና ሰበበ መንስኤውን የሚዘረዝር አንድ ደብዳቤ ለአፄ ምኒሊክ ሰደዱ ክሪስ የተሰኘው ታሪክ ጸሐፊ ስለዚሁ ደብዳቤ ሲያወሳ ‹‹. . ታዬ በሜይ 1907 ቁጭት የተሞላ ደብዳቤውን ለአፄ ምኒሊክ የጻፈው በዚህ መልክ ነበር ‹‹እኛ ሀበሾች በመንፈሳዊና በስጋዊ ጥበብ ወደፊት የማንገፋበት ምክኒያት ምን ይሆን ብሎ የሚጠይቅ . . ሕዝቡ ሁሉ ባይማርና የወንጌልን ስብከት በብዙው ባይሰማ እውነተኛ አውቀትና አፍቅሮት ቢስ ትህትና ቢጠፋ ነው. . በአገራችን ጥቂት እውቀት ያላቸው ሰዎች በመክበር ፈንታ ስለሚሰደቡና ስለሚዋረዱ ስለሚጠቁ የሚያውቁትንም ጠቃሚ የጥበብ ሥራ ትተው በቦዘን መኖር መረጡ፡፡›› በማለት ከተናገረ በኋላ ንጉሱ በጉዳዩ ላይ አጥብቀው እንዲያስቡ ችግሩንም ከፍጻሜው እንዲያደርሱ በመጠየቅ ይደመደማል ሲል ጽፎዋል፡፡ ክሪስ ያልጠቀሰው ቀሪ ክፍል እንዲህ ይነበባል፣

‹‹የአዳም ልጆች ዓለሙን ሁሉ የፈጠረ አድልዎ የሌለበትን አንድ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ላንዱ ወገን ሕዝብ ሙሉ ፣ላዱ ወገን ጎዶሎ ልብ አልፈጠረም በፍጥረቱም የአዳምን ልጆች ሁሉ አስተካክሎ እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል እንዲህ ከሆነ ስለምን የአውሮፓና የእስያ ሰዎች ከአፍሪካ ክፍልም ጥቂቶች ብልሃተኞች ሲሆኑ እኛ ሀበሾች መጽሐፍ ቢማሩ ኮቸር ለቃሚ . . .ብርና ወርቅ ቢሠሩ ቀጥቃጭ ቡዳ እንጨት ቢሠራ አናጢ እንጨት ቆርቋሪ . . . ቆዳ ቢፍቅ ጥንበ በላ ፋቂ እየተባለ ለሥራው ሁሉ ስም እየተሰጠ ስለሚሰደብ የጥበብ ሥራ ከጊዜ እየቀዘቀዘ ጠፋ ስለዚህ ጉዳይ ጃንሆይ አስበውበት እንዲህ ያለው ስድብ ሁሉ ባዋጅ እንዲከለከል . . . ሰዎች እንዲያከብሩ ቢያደርጉ . . . በሌላ መንግሥት ስምና ምልክት የተቀረጸ ገንዘብ ከመገበያየት በጃንሆይ መልክና ስም የተቀረጸበትን ገንዘብ እንዲወጣ ቢያደርጉ ነጻ መንግስትም ራሱንም የቻለ የተሟላ ይሆናል. . .››
ታሪክ ጸሐፊው ክሪስ እንደሚለው የታዬ ድበዳቤ ከተጻፈ ከ4 ወር በኋላ ማለትም በጃንዋሪ 1908 አፄ ምንሊክ የትምህርትን አስፋጊነት የሥራን ክቡርነት ያካተተውን አዋጅ አሳወጁ፡፡
ከጀርመን ምለስ ሦስተኛውን የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ኒሻን የአጼ ምኒልክ ዘንድ የተሸለሙት ታዬ ወደ ትውልድ አገራቸው በመዝለቅ ሥራቸውን ቀጠሉበዚያም ከተሰጣቸው ጉልት ገሚሱን በኃይል በመንጠቅ ቀሪውን ለመጠቅለል ያሰቡት ደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ባለጋራ ሆነው የተነሱባቸውን በጊዜውም የቤግምድር ገዢ ለነበሩትም ለንጉሥ ወ/ጊዮርጊስ እንዲህ ብለው ጻፉላቸው አለቃ ታዬ ሃይማኖቱ የንስጥሮስ ነው ይህንንም ሃይማኖት ለሕዝቡ ያስተምራል፡፡›› ንጉስ ወ/ጊዮርጊስ ብስጭት በሞላበት መንፈስ የሚከተለውን ደብዳቤ ለአለቃ ታዬ ሰደዱ፣

‹‹የተላከ ከራስ ወ/ጊዮርጊስ ይድረስ ከአለቃ ታዬ እንዴት ሰንበትሃል እኔ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ ዝም ብለህ ተቀመጥ ስንልህ እንደዚህ ያለ ትምህርት ከየት ያመጣኸው ነው? በምን ጠላኸኝ እንዳትል በ1903 ዓ.ም ኀዳር 24 ከን ተጻፈ ፡፡››አለቃም ድብዳቤው እንደደረሳቸው ሃይማኖታቸው ተዋህዶ መሆኑንና የተፈጸመባቸውም ግፍ አግባብ እንዳይደለ ለንጉስ ወ/ጊዮርጊስ በመግለጽ የተወሰደባቸውም መሬት እንዲመልሱላቸው ጠየቁ ንጉሱምደጃዝማች ወርቄን አስጠርተው የወሰዱባቸውን ጉልት ለአለቃ እንዲመልሱላቸው ፈረዱ ሁኔታው ያልተዋጠላቸው ደቻዝማች ወርቄም ‹‹ታዬ ሃይማኖቱ ፀረ ማርያም ነውና ሃገር መግዛት አይገባውም፡፡ አይደለሁም ካለም ሥዕለ ማርያም ይምጣና ይስገድ፡፡ በማለት ሌላ ሌላ ክስ ከፈቱ፡፡ ሥዕለ ማርያም መጣ ታዬም እንዲሰግዱ ታዘዙ እሳቸውም በዘጸአት 22፤1-5 ያለውን ክፍል ጠቅሰው ለሥዕል መስገድ እንደማይገባ በማብራራት ምላሽ ሰጡ ያንጊዜም በአደባባይ የተሰበሰበው ሕዝብ ቁጣ ገነፈለ የአለቃን ነፍስ ከሥጋዋ ለመነጠል ገሚሱ ጎራዴውን ሲመዝ የተቀረው ሽጉጡን ነቀነቀ የታዬን እምነት ያበሳጫቸው ንጉሥ ወ/ጊዮርጊስ ጉዳዩ ሃይማት ነክ በመሆኑ ታኀሳስ 24/1903 ክሱን ወደ አቡነ ማቴዎስ መሩት ጥር 28 በዋለው ጉባዔ አለቃ ፈለቀ ከሳሽ ሆነው በመቅረብ እንዲህ ሲሉ በጉባዔው ፊት አብራሩ ‹‹ለሥዕልና ለመስቀል አይሰገድም በሞቱ ቅዱሳን አማላጅነት አያምንም ዝክርና ምፀዋት የሞተ ሰውን ሊያጸድቅ እንደማይችል ይናገራል የልማድ ጾም ዋጋ እንደሌለው ይሰብካል ቀናትን አያከብርም፡፡ በቀረቡት ክሶች ላይ ከፍ ያለ ክርክር ከተደረገ በኋላ አለቃ ታዬን ለመርታት የሚያስችል በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ባለ መኖሩ ጳጳሱ ከባልደረቦቻቸውና ከመኳንቱ ጋር መክረው ለወደፊቱ ይህን ትምህርት እንዳያስተምሩ ገስጸው ለቀቋቸው፡፡ በአለቃ ታዬ መለቀቅ የተበሳጩት ካህናት በጊዘው የአፄ ምኒልክ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ተሰማ በማመልከት ያለ ሕግ ከታላቁ ወኅኒ ቤት እንዲገቡ አደረጉ፡፡ አለቃ ታዬ ወኅኒ ቤት ታስረው ከከረሙ በኋላ ተፈቱ፣ከዚያም በመጀመርያ ከደጃዝማች ሙሉ ጌታ፣ ቀጥሎም ከደጃዝማች ይገዙ ሀብቴጋር በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ በመጨረሻም በ1912 ዓ.ም ለመንግስት አማካሪነት ተመርጠው መስራት ጀመሩ ምሁር ታዬ የሕይወት ዘመናቸውን ከድካምና ከእንግልት ጋር ካሳለፉ በኋላ ነሐሴ 15 ቀን 1916 ወደ ዘላለማዊ ማረፊያቸው አቀኑ፡፡

ብርሃን መፅሔት
ቁጥር 36

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox