ዮሴፍ የሁለተኛ ልጁን ስም ኤፍሬም ብሎ ነበር የጠራው እንዲህ ሲል ፦ “እግዚአብሔር በመከራዬ አገር ፍሬአማ አደረገኝ”።(ዘፍ 41 ፡ 52) ዮሴፍ የቀረዉን ሕይወቱን የኖረው መከራን በተቀበለበት ምድር ነበር።”መከራ” ትርጉሙ ብዙ ነው፤ ስቃይ፣ ችግር፣ ሸክም፣ እና ፈተና ማለት ነው። ህመም እና አደጋ ማለት ነው። በጭንቅ የተሞላ ማለትም ነው። ይህ “የመከራ አገር” ዮሴፍ እግዚአብሔርን እና ህዝቡን ያገለገለበት ነው፤ እግዚአብሔር ወደዚህ አገር ልኮታልና። ይህ አገር እግዚአብሔር እርሱን ፍሬኣማ ያድረገበት ምድርም ነው፤ “የመከራዬ አገር”።
የዮሴፍ ልምምድ በአሁን ሰአት በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ ተስፋፍቶ ከሚገኘው አመለካከት ፍጹም ተቃራኒ ነው። ዛሬ ብዙዎች “የምቾት ሕይወት” የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ሕይወታችንን እና ስኬታችንን ከሌሎች ሕይወት እና ስኬት ጋር እንድናወዳድር የሚገፋፋ ነው ፤ ችግርን መከራን እና ፈተናን እንደ ውድቀት የሚመለከት አስተሳሰብ ነው። ይህ ሌላ ወንጌል ነው።
ይህ ለጆሮ የሚስማማ ስብከት ሁሌም ሰዎችን ወደ ሌላ አገር፣ ወደ ሌላ ከተማ፣ ምቾት ብቻ ወዳለበት ቦታ የሚመራ ነው። ይህ ልዩ ወንጌል፥ ከጽናት ይልቅ መመሳሰልን፤ ከባለአደራነት ይልቅ ባለቤትነትን፣ ከጥራትም ይልቅ ብዛትን የሚያበረታታ ነው።
የብዙ ክርስቲያኖች የእሴት ስርዓት በእጅጉ የተመታ ነው። ብዙዎች የሚሉት “የወንጌል ለውጥ” ወይም ደግም “ባህላዊ አግባብነት ያለው” ወደ መሆን መምጣት እውነት ቢሆንም ነገሩ ግን ከዚህም ያለፈ ነው። የእሴት ስርዓታችን እየተለወጠ ነው። ይበልጥ የሚያስፈራው ደግሞ በምድራችን ያሉት ትልልቆቹ የመገናኛ ብዙሃን እለት እለት የሚመግቡን ይህን አመለካከት መሆኑ ነው። አብዛኞቹ የክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና መጽሔቶች የሚያስተዋዉቁት በቅርቡ ሊደረጉ ስላሉ የብልጽና፣ ተጽእኖን የማስፋት፣ እራስን የማስተዋወቅ ወይም በወቅቱ ታዋቂ በሆነ ጉዳይ ላይ የሚደርጉ ኮንፍራንሶችን ነው። ክርስቲያኖች የስኬትን ቁልፍ ፍለጋ ወዲህ እና ወዲያ ሲሉ ከቦታቸው ጠፍተዋል። ይህንን የተበረዘ፣ ምቾት ይሚሰጥ፣ እና አለማዊ የሆነ ልዩ ወንጌል እግዚአብሔር አብ ከላይ ምን እንደሆነ ያያል፤ ይህንንም ዘመናዊ ክህደት ያለ ህሊና የሚሰብኩ ባልዳኑት ዘንድ ተናጋሪ የተባሉ ዝነኛ አገልጋዮችንም ይመለከታል። ይህ የሚጣፍጥ፣ ርካሽ እና ቀላል የሆነ ወንጌል ነው።
እግዚአብሔር አምላክ በዚህ ዘመን አይኖቻችን ለይተው ያዩ ዘንድ ጆሮዎቻችን ለይተው ይሰሙ ዘንድ ይርዳን።
በዚህ አለምን በመምሰል፣ እንደ አለም በመመላለስ፣ እና ከአለም ጋር ወዳጅ በመሆን አለም ጋር ለመድረስ በምናደርገው ዋጋ የሚያስከፍል ሩጫ እኛ እራሳችን አለምን ሆነናል። ከረዥም ጉዞ ድካም የተነሳ እያሽከረከረ እንደሚታኛ ሹፌር ሆነናል ፤ ሳምሶን ደሊላ ታፋ ላይ እንደተኛው። ይህም ብዙዎችን እንደ ሳምሶን ጥንካሬአቸውን እና ራዕያቸውን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። እሴቶቻቸውን ለድርድር ያላቀረቡትን፥ ዮሴፍን፣ ጳውሎስን፣ ኤርምያስን፣ እና ኢየሱስ ክርስቶስን አስቡ።
ለዚህ የምቾት ወንጌል እጅ የሰጡ አማኞች መቼም ቢሆን እረፍትን አያገኙም፤ ከምድረ በዳው በስተጀርባ ያለውን ውበትም አያዩም፤ ከእራስ ይልቅ ከፍ ወደሚለው አለት ላይም አይወጡም። በመከራችሁ አገር የእምነትን ውጊያ ለመዋጋት የወሰናችሁ ክርስቲያኖች አናንተ ግን መከራው ነፍሳችሁን እንደቀረጻት ታያላችሁ፤ ትለወጣላችሁ ያለ “መከራዪ አገር” እንደዚህ መሆን አልችልም ነበር የምትሉትን ሰውም ትሆናላችሁ።
ምንም እንኳን የዮሴፍ ፍጻሜው አንድ እጅግ ከፍ ያለ ደርጃ እና የከበረ ቢሆንም፤ ወደዚህ እግዚአብሔር ቃል ወደገባለት ፍጻሜው ለመድረስ ግን በ “መከራው አገር” አልፎ እንደነበር መዘንጋት የለብንም።
Copyright Hiyawkal © 2025
Leave a Reply