በዚህ እትማችን በወጣቶች ዙሪያ አንዳንድ ነጥብ በማንሳት ሐሳቦችን አንሸራሽረናል፡፡ በተለያየ ቦታ እንደ ትኩስ ኃይልነቱ የሚጠቀሰው ወጣት የበጎውንም ሆነ የክፉውን ዓለም ታቃፊ እንዲሆን ብዙ ጥሪ ይቀርብለታል፡፡ የዕድሜው ክልል ከአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ይዘቱ አኳያ ሩጫ የበዛበት ስለሆነ ለሕይወት ዘመኑ የሚሆን መልካምም ሆነ ክፉ ስንቅ ሊሰንቅበት ይችላል፡፡ ሰማያዊው ጥሪ የሚበጀውን የከበረ ሕይወት ሲያሳየው የጨለማው ጥሪ ደግሞ በዙሪያውያለውን ዓለማዊ እንቅስቃሴ የራሱ ሳያደርግ ዕድሜው እንዳይተላለፍ ያባብለዋል፡፡ ገሚሱ ዓይኑ በርቶለት ሲያርፍ ገሚሱ ደግሞ በክፉው ተተብትቦ ይገኛል፡፡
ብርሀን በርቶላቸው ጉልበታቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር እንደሆነ የተገነዘቡቱ በእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ጉልህ ሚና ሲጫወቱ እንመለከታለን፡፡ ሩጫ ሲበዛ እንቅፋት እንደሚበዛ ሁሉ የወጣትንት ዘመንም የራሱ የሆኑ እንቅፋቶች አሉት፡፡ ለቤተክርስቲያን ባላደራ የሆኑት ቋሚ ሐብቶች እንግዲህ እንዴት ባለ ሁኔታ ነው ተይዘው የሚገኙት? የወጣቱ ጥያቄ ፍላጎትና ችግር ምን ይመስላል? የሚሉት ጥያቄዎች በመያዝ ከወጣት ታጋሽ ሳህሉና ከወጣት ውቤ ሰለሞን ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡
ወንድም ታጋሽ ሳህሉ በአዲስ አበባ መካነ ኢየሱስ የወጣት አገልጋይ በወጣት ለክርስቶስ አገልግሎት የመዘምራን አባል በቃል እግዚአብሔር አንባቢያን ማኅበር የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ እና በአሴምብሊስ ኦፍ ጋድ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን እህት ውቤ ሰለሞን ደግሞ በቀበና ገነት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነች፡፡ ወደ ቆይታችን እናምራ፡፡
ብርሃን፡- የወጣቶች አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ምን ይመስላል?
ታጋሽ፡- የወጣት አገልግሎት ስንል አንዳንድ ጊዜ የተደበላለቀ ነገር ይታያል፡፡ በትክክለኛ የወጣትነት ዕድሜ ክልል ያለው በርካታ ሆኖ እያለ በጉልምስና የዕድሜ ክልል ያሉ ወገኖች የወጣቱን ስፍራ በመያዝ ለሌላው ቦታ የሚዘጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ አካሄድ
ደግሞ አገልግሎቱ ተፈላጊ ደረጃ ላይ እንዳልደረሰና ወጣቱንም እናዳላፋፋው ያመለክታል፡፡
ውቤ፡- የወጣትነት አገልግሎት በቤተክርስቲያን በጣም ሰፋ ያለውን ቦታ ይዞ አመለክታለሁ፡፡ ከምእመኑ አብዛኛው ወጣት ሲሆን በየአገልግሎቱም ተካቶ እናየዋለን፡፡
ብርሀን፡- በቤተ ክርስቲያን ያለው ወጣት መሰረታዊ ጥያቄው ምንድን ነው ?
ውቤ፡- ወጣቱ በጥያቄ የተሞላና ፈልጎ ገና ያልጠገበ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ አገር አቀፍ በሆነው ነገር በማኅበራዊ ደረጃ የሚደርሰው ችግር ሁሉ ሲነካው ይታያል፡፡ ከችግሮቹም መካከል ሥራ አጥነት በቂ ትምህርት ያለማግኘት የኑሮ መዛባት በጊዜው ትዳር
ያለመያዝ ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ማኅበራዊ ቀውሶች የተነሳ አንድ ወጣት ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣ ችግሮቹ ቶሎ እልባት እንደሚያገኙለት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍቅርን ይራብና ይመጣል በቤተ ክርስቲያን ግን ፍቅርን የሚያሳየው ሊያጣ
ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ሊረበሽ ይችላል፡፡ መንፈሳዊም ረሀብ ስላለ ብዙ ፈልጎ ይመጣል ጥሩ መጋቢ ሳያገኝ ሲቀር ደግሞ የአመፀኛነት ሁኔታ ሊያሳይ ይችላል፡፡
ታጋሽ፡- አገልግሎትም ሲፈልግ እንመለከታለን፡፡ በአንዳንድ ቦታ ሥልጠና ይሰጠውና ወደ አገልግሎት እንዲሰማራ አይደረግም፡፡ በሮች ሲያጣ ሌላ በር ፍለጋ የሚሄድበትም ሁኔታ አለ፡፡ እህቴ እንደጠቀሰችም የሥራና የትምህርት ችግሮችም አሉ፡፡ ቤተ
ክርስቲያን የማገልገል እና የመሥራት ዕድል እንዲከፈትላቸው ሲሹ ይታያል፡፡ አንዳንዶች ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ከቤተክርስቲያን ተለይተው መጋቢ (ፓስተር ) እየተባሉ ሌሎች ወጣቶችን ሲሰበስቡ ይታያሉ፡፡
ብርሀን፡- ወጣቶች ከመሰረታዊ ፍላጎታቸው አንፃር እንዴት መያዝ አለባቸው ብላችሁ ታምናላችሁ?
ታጋሽ፡- ትልቁ ማሰሪያ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅርን የሚራብ ሰው ሲያገኝ ይረካል፡፡የእግዚአብሔርም ቃል የሚያዘን ይህንኑ ነው፡፡ ሌላው እንግዲህ የወጣቱ ፍላጎትን አቅጣጫ የሚያሲዝ አሰራር ሊኖር ይገባል፡፡ በአንድ ነገር ላይ ያለመርጋት ችግር ይታያል፡፡ አንድ ጊዜ
አንድ ሰው መራ ማለት ሌላውን ትከሻው ላይ አስቀምጦ በሩቅ የሚያሳይ ሰው ነውሲሉ ተናገሩ በሩቅ ያለውን በደንብ ሊመለከት የሚችለው አቃፊው ሳይሆን በትከሻ ላይ የተቀመጠው ነው፡፡ አሻግሮ የተመለከተው ነገር ደግሞ በሕይወቱ እውን እስኪሆን ድረስ
እርካታን አያገኝም፡፡ ያሳየውን ሁሉ እንዲደርስበት መንገዱን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ እንደ የደረጃቸው ትምህርት መስጠትም አሰስፈላጊ ነው፡፡ ወተት ለሚያስፈልገው ወተት አጥንትም ለሚያስፈልገው አጥንት መስጠት ይበጃል፡፡ ሲፍገመገምና ሲወድቅ
ልንደግፈውና ልናነሳው ይገባል፡፡ ሁሉ እኩል አይሄድም ሁሉም እኩል አይራመድም ሁሉም ግን የአካሉ ብልትና አገልጋይ ነው፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ ‹‹ማንም ታናሽነትህን አይናቀው›› ሲል የታናሽነቱ ጉዳይ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ያመላክታል፡፡
የጳውሎስ ሀሳብ ብቁ የተደረክ ስለሆነ ወደፊት ተራመድ የሚል ነው፡፡ ሌላው ሁሉ የእኛን አካሄድ ይከተል ማለቱ አግባብ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ የራሱ ቅኝት እንዳለው ልብ ማለት ይኖርብናል፡፡ ከተለያየ ኑሮ መስክ (ሴተኛ አዳሪነትን ጨምሮ) የሚመጡ
ወጣቶች እንዳሉ በመገንዘብ ፍሬ ሊያፈሩ በሚችሉበት ሁኔታ መያዝ ጠቃሚ ነው፡፡
ውቤ፡- ለወጣቱ ፍቅር መስጠት፣ቦታን መስጠት ፣ በዕውቀት ታንፀው እንዲያድጉ ማድረግ ፀጋቸውን መቀበል ፍላጎታቸውን ማወቅና እንደየፍላጎታቸው ተገቢ በሆነ ሁኔታ ማድረስ አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ አስባለሁ፡፡ ዳዊትን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡
ለሰልፍ ልውጣ ባለበት ጊዜ ወንድሞቹ አልተቀበሉትም ነበር፡፡ በጊዜው እግዚአብሔር ዳዊትን በተመለከተበት ዓይን ወንድሞቹ አላዩትም እስራኤል እንዲያርፍ ግን ዳዊት በዚያ ሁኔታ ማለፍ ነበረበት፡፡ ቤተክርስቲያንም ወጣቶችን በጌታ ዓይን
እየተመለከተችና ፀጋቸውን እየለየች ልታበረታታቸው ይገባል፡፡ሌላው እንግዲህ ጳውሎስ ጢሞቲዎስን በምክር በማስተማር ኃላፊነትን በመስጠት እንዳሳደገው ቤተክርስቲያንም ያበላሻሉ ብላ ከማሰብ ይልቅ የሚሠሩ ሰዎች አድርጋ ማብቃቷ አስፈላጊ ነው ብዬ
አስባለሁ፡፡
ብርሀን፡- የማማከር አገልግሎት ለወጣቱ ምን ያህል ያስፈልገዋል ትላላችሁ ?
ውቤ፡- ወጣቶችን የማማከር አገልግሎት በቤተክርስቲያን ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት አናይም አገልግሎቱ አለም ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል፡፡ ወጣቱ ደግሞ የምክር አገልግሎት ከማንም የበለጠ ማግኘት ይገባዋል፡፡ በባሕሪው ገና ያለረፈ ስለሆነ የሚያሳርፍ ምክር
ከቤተክርስቲያን ይፈልጋል፡፡ ምርጫ የሚያደርግበት የሚወስንበት ብዙ የተለያየ መልክ ያላቸው ዕድሎችም የሚያጋጥሙበት ስሜቱ የሚረበሽበትና በሚያያቸው ነገሮች የሚወስድበት የዕድሜ ክልል ላይ ስለሚገኝ ሚዛን የጠበቀ አካሄድ ለመሄድ ይቸገራል
ዕድሜዬም ሳይገፋ ብሎ ቶሎ አንድ ነገር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ቃል የበሰሉ ሊጠቅሙት የሚችሉ ከገኑ የሚቆሙና የውስጡን ጥያቄ ተረድተው የሚያደምጡት አማካሪዎች ያስፈልጉታል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል መካሮች በበዙበት ብዙ ድል አለ ስለሚል በምክር አገልግሎት የሚያልፍ ወጣት ስኬታማ ይሆናል፡፡ በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ሁልጊዜ ጥያቄና መፍትሄ አልባ ችግር የሚበቅለው ጠጋ ብሎ መሪ እና አማካሪ ሰለማይኖር ይመስለናል፡፡
ታጋሽ፡- አብዛኛው እንዲሁ እየተመመ የሚሄድ ነው የሚመስለኝ፡፡ መካሪ እና ደጋፊም በሌለበት ሁኔታ ብዙዎች ፀንተው መመልከት የሚያስደስት ነው፡፡ አገልግሎቱም ካለመኖሩም የተነሳ ተሰነካክለው የወደቁም አሉ፡፡ ወጣቱ ሕመሙን የሚያክምለት ሰው
ይፈልጋል፡፡ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ብንመለከት ወጣቱ በውስጡ ችግር እያለበት በውጪም ያለው ነገር ፍላጎቱን የሚያረካ አይደለም፡፡ ይህንን ወጣት ቤተክርስቲያን ማሳረፍ መቻለ አለባት፡፡
ብርሀን፡- አንዳንድ ወጣቶች ቤተክርስቲያናቸውን ጥለው ይወጣሉ፡፡ በአብዛኛው ችግሩ የመሪዎች ነው ወይስ የወጣቱ?
ታጋሽ፡- ወጣቱ ተወቃሽ ነው የምልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ነገሩ ሁሉ የውሃ መንገድ ይመስላቸውና ተገላቢጦሽ ሲሆን አቅጣቸጫቸውን ይለውጣሉ፡፡ ትዕግስት ፀሎትና የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፡፡
የቤተክርስቲያን መሪዎችም የሚወቀሱበት ሁኔታ አለ የወጣቱን ተፈጥሮ ግንዛቤ ያስገባ መርሐ ግብር ከሌላቸው የወጣቱን ልብ ላይዙት ይችላሉ፡፡ የአገልግሎት ሸክምና ናፍቆት በውስጥ እየተቀጣጠለ ወዲያው በር ላይከፈት ይችላል፡፡ ይኼኔ አንዳንዱ
በውስጡ ያለውን ነገር ለማስወጣት ሌላ በር ፍለጋ ይሄዳል፡፡ ይሄ ችግር የወጣቱ ብቻም እናዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡መሪዎች ከመንጋው በልጠው በማይገኙበትም ጊዜ ችግር ይጠራል፡፡ የማስቀደም ነገር ቢኖር መልካም ነው፡፡ በአንድ ቤተክርስቲያን
አንድ የወጣት መሪ ነበር፡፡ ወጣቶቹ በቁጥር አነስተኛ ነበሩ፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ እያደገች ስትመጣና ብዙ ወጣቶች ስታቅፍ መሪው እድገት አያሳይም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አገልግሎቱን ለሌላ ሰው እንዲለቅ ተደረገ እንዲህ አይነት አሠራሮች ቢኖሩ
ችግሮች ይቀረፋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ መሪው የጌታ ፀጋ የሚታይበት ሰው መሆን አለበት፡፡ ወደ ዓለም ሚመለሱትን ስንመለከት በጌታ ኢየሱስ ጊዜም ተመሳሳይ ችግር ነበር፡፡ ዘሩ በጭንጫ መሬትና በሾህም ላይ ይወድቃል ከመጀመሪያውም ያልተመሠረቱት
ቢሄዱ አይደንቅም እኛ ግን መጠንቀቅ ያለብን በቂ ምግብ ካለማግኘታቸው የተነሳ ስለሚሄዱቱ መሆን አለበት ዓለም የምታሳየው ነገር አለ እግዚአብሔርም ደግሞ የሚያሳየው ነገር አለ ቤተክርስቲያን እንግዲህ መታየት ያለበትን ነገር ሁሉ ማሳየት
ይኖርባታል፡፡
ውቤ፡- ወጣቱ አዲስ ነገር የመፈለግ ባህሪ አለው፡፡ ራሱን የመምራት ብቃት ያለውም ስለሚመስለው ለሥርዓት እምብዛም ተገዢ አይደለም ዛሬ ብቻ የሚታይበትና ፍጥነትም ያለበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ እንግዲህ የቤተክርስቲያን እቅድ አውጥታ በዚህ መልኩ ተያዙ
ስትል ወጣቱ ደግሞ አካሄዱ ኋላ ቀር ይመስለዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ችግሮች ከመነሳታቸው በፊት እውነት በወጣቱ ውስጥ መሰረት እንዲጥል የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባት ነው የማምነው፡፡ ፍቅርን ማሳየት እባ ምሳሌም መሆን አለባት፡፡ አንዳንዱ
ጌታን እንጀራ ፈልገው እንደተከተሉት ሰዎች ሌላ አላማ ኖሮት ይመጣል ከተንከባካቢ እጦት ግን ወጣቶች እንዳይወቱ መጠንቀቅ አለባት፡፡
ብርሀን፡- ወጣቱ ትምህርትና ስራን በተመለተ ምን ማድረግ አለበት ብላችሁ ታምናላችሁ?
ውቤ፡- ርዕሱ ከባድ ነው ወጣቱ የስራን ክቡርነት ማመንና ከትንሽ ነገር ለመነሳት ጥረት ማሳየትን ማወቅ እንዳለበት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የትልቅ ነገር መነሻ ትንሿ ነገር ነች ያእቆብ ከበግ እረኝነት ተነስቶ ነው የሁለት ክፍል ሰራዊት ባለቤት የሆነው በቤተክርስቲያን
የሞያ መስክ ፈጥሮ በትንሽ ወጪ ብዙ ሰዎቸችን ማሳተፍ ይቻላል፡፡ በገንዘብ እጦት ትምህርትም ሆነ ስራ መስራት የማይችሉ ብዙ ወጣቶች ስላሉ በውጭ ሰዎች ሳይሆን በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ገንዘብ እንዲያዋጡ አስተባብሮ መርዳት ጥሩ ነው
እላለሁ፡፡ በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ ያልሰለጠኑትን የሚያሰለጥኑበት ሁኔታ ቢመቻችና ቤተክርስቲያብን ወጣቶችን ማደራጀት አገልግሎትም ብትሰጥ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ትምህርትን በተመለከተ የተማሩቱ ሌሎችን የሚያስተምሩበት ሁኔታ
መፍጠር ባለፈው ክረምት በኢቫሱ አስተባባሪነት በየቦታው ነፃ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ይህ ጥሩ ጅምርና ምሳሌ ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊው ነገር ላይ ማተኮሯ መልካም ቢሆንም ሁነኛ አገልጋይ ለማግኘት የሰውየው የኑሮም ሁኔታ መስተካከል
አለበት፡፡ የኑሮ ቀውስ አገልግሎትን እነደሚነካ መታሰብ አለበት፡፡
ታጋሽ፡- መደጋገፍ ይኖርብናል ወላጅ ልጁን የሚረዳበት መንፈስ በቤተክርስቲያንም ቢታይ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን ባቅሟ አንዳንድ የሙያ ማሰልጠኛ መስኮችን ብትከፍት ጥሩ ነው፡፡ ትልቁ እና መዘንጋት የሌለበት ነገር እግዚአብሔርን ተስፋ
የማድረጉ ጉዳይ ነው፡፡ አቅጣጫ የሚጠፋበት ጊዜም አለ፡፡ ዝናብም ሳይታይ ደመናም ሳይታይ ሸለቆው ውሃ እንደሞላ መፅሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በትእግስት መጠበቅ መልካም ነው፡፡ በጋራ ፀሎት የምናደርግበት አንድ
ኅብረት አለን፡፡ በግል ያጋጠመኝን ብጠቅስ መልካም ነው፡፡ አንድ ጊዜ ተነስቼ ትምህርት መማር እንደምፈልግ ገልጬላቸው ፀለየን ከዚያ በኋላ ዓመት አለፈ ሁለተኛውም አለፈ፡፡ በሦስተኛው አመት ግን አግዚአብሔር በር ከፈተልኝ የጌታን ፊት በፈለግን
መጠን የእርሱ የሆነውንና የሚያረካንን ነገር ነው የምናገኘው ጥሩ ነጋዴ ለመሆን ፈልጌ ሞክሬ ነበር ያ መንገድ ግን ለእኔ ተገቢው መንገድ አልነበረም፡፡
ብርሀን፡- ጋብቻን በተመለከተ ወጣቱ ምንያሻዋል ትላላችሁ?
ታጋሽ፡- ብዙ ቦታ የመቀራረብ ችግር አለ በቤተክርስቲያን የሚደረግ አገልግሎት አንዱ የመቀራረብ መንገድ ነው፡፡ በአንዳንድ ቤተክርስቲያን በጋራ ለየት ያለ ሥፍራ የመሄድ ሁኔታ አለ፡፡ አላማው ወጣቶችን ለማስተዋወቅ ባይሆንም እንኳን እርስ በእርስ
የመቀራረብን አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በቡድን በቤተክርስቲያን በኩል ሽርሽር ቦታ ሄዶ ማሰለፍ አግባብ አይደለም ቢሉም እኔ ግን ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሌላው ቤተክርስቲያን ውስጥ ክበብ ቢፈጠር ጥሩ መገናኛም ጊዜ ማሳለፊያ ይሆናል፡፡ ራቅ
ያለ ቦታ ሄደው ጊዜ ከሚያሳልፉ ይልቅ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ የትዳር ጓደኛን በመፈለግ የሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት በጥንቃቄ መታየት አለበት እላለሁ፡፡ እኔ ባለሁባት ቤተክርስቲያን የጎልማሶች ፕሮግራም ይደረጋል
የተለያዩ መንፈሳዊ ጉዳዮች የሚነሱ ሲሆን አንዱም ጋብቻ ነው፡፡ ጎልማሶቹም እንዴት እንደተገናኙ እና እንደተጋቡ ይናገራሉ፡፡ ለሌላው ጥሩ ልምድ የሚሆኑ ሀሳቦች ስለሚንሸራሸሩ በሌሎች ቦታዎችም ቢታሰብባቸው ተቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ብርሀን፡- በመጨረሻ የምታስተላልፉት መልእክት ካለ?
ውቤ፡- ሐና ለሳሙኤል ያየችውን ራእይ ቤተክርስቲያን ለወጣቶች ብትመለከት መልካም ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እግዚአብሔር የሚመለከተውን መንገድ አብሮ መመልከት ይሆናል፡፡ ወጣቶች ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን የወንጌል በር ለሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ
መሪዎች ስለሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋልጋቸዋል፡፡ ዘላቂ የቤተክርስቲያን ሐብትም ናቸው፡፡
ታጋሽ፡- ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ትቀፍ ትንከባከብ ገንዘብም ታድርጋቸው፡፡ ወጣቱም ደግሞ ከሁሉም በፊት በእግዚአብሔር ላይ የሚያርፍና እንደ ዕንባቆምም በመጠበቂያው ላይ ሆኖ እግዚአብሔር የሚያመለክተውን ነገር እያየ ቢንቀሳቀስ የሚበጀው ይሆናል፡፡
ብርሃን መፅሔት
1989 ቁጥር 27
Copyright Hiyawkal © 2024
Leave a Reply