ታህሳስ 7 1941 ፤ ጃፓን ፐርል ሃርበር በሚባል ቦታ አሜሪካ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት አድርሳ ነበር ።ይህ በፓሲፊኩ የጦር ክፍል ላይ በደረሰው ጥቃት ሀገራችን 2403 ዜጎቻን አጣች።በቀጣዩ ቀን ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጥቃቱ በአሰቃቂነቱ እና አሳፋሪነቱ የሚታወስ ነው ሲሉ ለሀገሪቱ ተናገሩ። ያም ጥቃት አሜሪካ 4 አመት ለቆየ እና 400,000 ዜጎቿን ላሳጣት አለምአቀፋዊ ግጭት ውስጥ ገፍትሮ አስገባት።
አሜሪካ ጦርነት ውስጥ ገባች። የምልመላ ማስታወቂያዎች በየቤቱ ፖስታ ሳጥን ውስጥ መድረስ ጀመሩ። እናቶች ለልጆቻቸው የተላከውን የምልመላ ወረቀት ሲያዩ የሚሰማቸውን አንጀት የሚያላውስ ስሜት መረዳት ይቻላል። በእርግጥ አላማው ፍትሃዊ እንደሆነ ያውቃሉ ግን ልጆቻቸው ሁሌም ልጆቻቸው ናቸው። ምንም ያህል ምክነያታዊ እና አስገዳጅ ውጊያ ቢሆን፤ ይህን ትልቅ መስዋዕትነት መክፈል የሚያስክትለውን ጭንቀት መካድ አይቻልም።
በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ሲጋፈጡት የነበረው እውነታ ይህ ነበር፤ በተለይም በደቡብ ካሮላይና ሴነካ ከተማ በሚገኝው ኡቲካ የጥጥ ማምረቻ ኮረብታ ተብሎ ይጠራ የነበረው አካባቢ ይጠቀሳል። አካባቢው ሁሉም ሰው ከሚሰራበት የጥጥ ማምረቻ እና ከሚካፈሉበት አንድ ቤተክርስቲያን የተነሳ እጅግ የተያያዘ ማህበረሰብ ነው። እነዚህ ቤተሰቦችም በህብረት ልጆቻቸውን ወደ ጦርነት ይልኩ ነበር። እናቶች እና አባቶችም በአስቸጋሪ የህይወት ምእራፍ አይን ሊጣልበት ወደሚችለው ወደ እግዚአብሄር ዘወር ብለው ነበር።
ስለልጆቻቸው በመጸለይ በስውር ነፍሶቻቸውን ለእግዚአብሄር የሚያፈሱበት ቦታንም ይፈልጉ ነበር። ከመንደሩ ወጣ እንደተባለ፣ የመቃብር ቦታን አልፎ እንዲሁም ስምጥ ቁልቁለቱን ወርዶ ከጅረት አጠገብ ሸክማቸውን የሚያራግፉበት መሰዊያ ለጌታ አቆሙ።
ለእነዚህ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሰዎች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ስለልጆቻቸው የከበደ ልብን ይዞ መነሳት የየቀኑ ክስተት መሆን ጀመረ። ከስራ በኋላ፤ ለመጸለይ ወደ ጫካ ውስጥ ይገባሉ። በመንገድ ላይ እየሄዱ እያሉ ያለባቸውን ሸክም የሚወክል ድንጋይ ያነሳሉ። ድንጋዩንም ወደመሰዊያው ወስደው ይጥሉትና እስከ ምሽት ደረስ ለሰአታት ይጸልያሉ። ልጆቻቸው በባእድ ምድር ሲዋጉ አባቶች ደግሞ በጸሎት ይዋጉ ነበር።
የጸሎትን ሃይል መካድ አይቻልም። አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ በተሳተፈችባቸው 4 አመታት ከዚያ ኮረብታማ መንደር የሞተ አንዳች ሰው አልነበረም። ሁልም ልጆች ወደ ቤቶቻቸው በሰላም ተመልሰዋል።
በ1945 ጦርነት የተፈጸመ ቢሆንም የመሰዊያው ልምድ እንደቀጠለ ነበር። በየቀኑ ለፈውስ እና ነጻ ለመውጣት ይጸልዩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሸክማቸውን ለመወከል የሚሸከሙት ድንጋይ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሌሎች ሰዎች በመሸከም ያግዟቸው ነበር። እውነትም አንዳቸው የሌላቸውን ሸክም ይሸከሙ ነበር።
ከሁሉ በላይ ለወዳጅ እና ለቤተሰብ መዳን የሚጸለየው ጸሎት የጸና ነበር። በየቀኑ ለተሃድሶ በጸሎት ይተጉ ነበር። እግዚአብሄርም ለ አንድ አስርት አመታት በመሰዊያው ላይ የተጸለየውን ጸሎት በምስራቃዊው ዋና መንገድ ላይ በሚገኝው ቤተክርስቲያናቸው ላይ ተሃድሶን በመላክ መለሰው።
ቤተክርስቲያኗ ፈጣን የሆነ እድገትን ማየት ጀመረች። በአባላት ዘንድ ወዳጆቻችው እና ጎረቤቶቻቸው ሲድኑ የማየት ቀናት ነበር። ወንድ እና ሴቶች ወደቤተክርስቲያኗ በመምጣት ከተለያዪ ሱሶች ነጻ ይወጡ ነበር። በዚህ የእግዚአብሄር የስራ ወቅት በጥጥ ማምረቻው በተለያዩ ፈረቃዎች ይሰሩ የነበሩ ለስራ ባልደረቦቻቸው ወንጌልን የመሰክሩላቸው ነበር። ወንጌልን ከነገሯቸው በኋላም ስራ እንዳለቅ ወደ መሰዊያው ይወስዷቸው ነበር። የተሃድሶ መንፈስ በአካባቢው በሚገኙ በመንፈስ ቅዱስ የተሟሉ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋፋ።
ኤ.ስ ወርልይ እና በምስራቃዊው ዋና መንገድ ላይ የሚገኝው ቤተክርስቲያን መጋቢ የሆነው ጄ. ዊትሎው በቅርብ በምትገኘው በዋልሃላ ከተማ የተሃድሶ ማእከል ለመትከል ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በከተማዋ መሃል የሚገኝ የተምባሆ ማድረቂያ የነበር ያረጀ የእርሻ መጋዘን ተከራይተው አጽደተው ለአገልግሎት ዝግጁ አደረጉት። ምልክቶች ድንቆች እና ተአምራቶች የየቀኑ ክስተት ስለነበሩ ፡ በዙ ህዝብ ከደቡብ ካሮላይና ፣ ከሰሜን ካሮላይና እና ከጆርጅያ ይመጡ ነበር።
ወደ ትምባሆ መጋዘኑ እንደገባችሁ ከጥቅም ውጭ ሆነው ከጣራው ላይ የተንጠለጠሉ ካራንቾች ፣ ምርኩዞች ፣ ተሽከርካሪ መቀመጫ እና አልጋዎች ይታዩ ነበር። እነዚህ በቀድሞ ተጠቃሚዎቻቸው የማይፈለጉ “የጸጋ ዋንጫዎች” ናቸው። የእግዚአብሄርን የፈውስ ሃይል በዝምታ የሚመሰክሩ ነበሩ።
አንድ ጎልማሳ በተሽከርካሪ አልጋ በአምቡላንስ ወደ ተሃድሶው የመጣበት ምሽት ነበር። ከነበረበት ከባድ ካንሰር የተነሳ ለመኖር ጥቂት ቀናት እንደቀሩት ተነግሮት ነበር። ዶከተሮችም ለሞት አሳልፈው ሰጥተውት ነበር። በዚያም ምሽት መጋቢ ዊትሎው እያገለገል ነበር። ሰውየው ወደአዳራሹ ሲገባ ቢያየውም መጋቢው ምንም የመረበሽ ስሜት አይታይበትም ነበር። ከተማዋ ትንሽ ከተማ ስለነበርች ብዙ ሰው የሰውየውን ሁኔታ ያውቁ ነበር፤ ለሰውየውም የፈውስ ቀን ይሆንለት ይሆን እያሉ ያስቡ ነበር።
ወንድም ዊትሎው አገልግሎቱን እንደጨረሰ ወደሰውየው ቀጥ ብሎ ሄዶ “ብር እና ወርቅ የለኝም ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ በናዝሪቱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳ እና ተመላለስ” አለው። ወዲያውም ሰውየው ተፈወሰ። ከአላጋውም ላይ ተስፈንጥሮ ተነስቶ በጌታ ፊት ሃሴት አደረገ። ሰውየውም ረጅም እና ጤነኛ ህይወትን ከዚያ በኋላ ኖሯል።
የዚህ የሚገርም ተሃድሶ እናበሴንካ እና አካባቢዋ በመንፈስ የተሞሉ ቤተክርስቲኖች ፈጣን እድገት ምንጭ በዚያ ያረጀ የመሰዊያ አለት ላይ የቀረቡ ጸሎቶች ናቸው። በብዙ መንገድ እነዚያ አለቶች ማህበረሰቡን ለነቀነቀው ተሃድሶ መሰረት ናቸው።
በሚያሳዘን መልኩ ግን እነዚያ የመሰዊያ አለቶች ተረሱ። አመታት ባለፉ ቁጥር ለጸሎት ወደዚያ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እያነሰ እና እያነሰ ሄደ። ከዚያም በጫካዎች ውስጥ ተሰውሮ ተረሳ። በተመሳሳይ ሁኔታ በእነዚያ ቤተከርስቲያናት ውስጥ ይነድ የነበረው የነበረውም እሳት ቀዝቅዞ ጠፋ። ያሳፍራል።
በዚያ መሰዊያ ላይ ይሰበሰቡ የነበሩ የእግዚአብሄር ሰዎች ተሃድሶ እንዴት መፈለግ እንዳለበት አሳይተውናል። በየምሽቱ እየመጡ ይማልዱ ነበር። በጸሎት በእግዚአብሄር ፊት እንዴት መቆየት እንዳለባቸው ያውቁ ነበር፤ ከዚያም የተነሳ ጌታ በምልክቶች በድንቆች እና በተአምራት ይመልስ ነበር።
ወዳጄ ሆይ ፤ ዛሬ ተሃድሶ የዘገየበት ምክንያት እኛ በእግዚአብሄር ፊት መቆየት ስላልቻልን ነው። ተሃድሶ እንደ መልስ ነው የሚመጣው። ከተሰበረ እና ከተዋረደ ልብ ለሚጸልይ ጽኑ እና እውነተኛ ጸሎት የሚመጣ የሰማይ መልስ ነው። በእርግጥም እግዚአብሄር ሲሰራ ማየት የምንፈልግ ከሆነ ጠልቀን ማየት ያስፈልገናል። ተሃድሶ ሁሌም በመሰዊያ ላይ ይገኛል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፤ ከአራት መጋቢዎችና ከስድስት የተለያዩ ቤተ-ክርስቲያናት ከተውጣጡ አባላት ጋር በመሰውያው ድንጋይ ዙርያ በክብር ለመሰብሰብ እድሉን አግኝቼ ነበር። እነዚህ ቤተ-ክርስቲያናትን እርስ በርሳቸው ያገናኛቸው በዚሁ የድንጋይ ካብ ያላቸው ታሪክ ነው። በዛፎቹ ውስጥ ተገናኝቶ መጸለይንና የጠፉትን ማፈላለግ ተቀዳሚ ግባችን አድርገን ነበር። የመሰውያውን ድንጋይ ዳግመኛ ለመገንባት እንዲሁም የራሳችንን አዳዲስ ድንጋዮች ለመደረብ ነበር የመጣነው።
በዛች ከሰአት የጌታ ህልውና በቦታው እጅግ ሃያል ነበር። ለቅድስና እና የእግዚአብሔር ሰራዊት እንዲሳ በፊቱ ንስሐ ገባን። እግዚአብሔር በደቡብ ኬሮላይና ግዛት ዳግመኛ ተሐድሶን ያመጣ ዘንድ ጠየቅነው። በመሰውያው ከ80 አመታት በፊት የቀረበው ጸሎት ምላሽ አመጣ። ዛሬም ቢሆን መልስ ለማግኘት የሚጠባበቁ ጥያቄዎች እንዳሉ ምንም ጥርጣሬ የለኝም።
በአቅራቢያቹ የተረሳ የመሰውያ ቦታ ይኖር ይሆን ብዬ አስባለው፣ የግድ በጫካ መካከል የሚገኝ የድንጋይ ካብ መሆን የለበትም። ምናልባትም በቤተ-ክርስቲያናቹ እየጠበቃቹ ይሆናል፣ በአልጋቹ ጎን ወይንም ይህን ጽሁፍ ሆናቹ ከምታነቡበት ስፍራ አጠገብ።
ወዳጄ ሆይ ፤ ተመልሰን መሰውያውን የምንሰራበት ግዜ አሁን ነው። ቀድሞ እግዚአብሔር በሀይል የተመላለሰበት አሁን ደግሞ የተበታተነዉን ስፍራ ዳግመኛ የምንጎበኝበት፣ የጌታን ሃሳብ የምናስታውስበት ግዜ አሁን ነው። አዳዲስ መሰውያዎችንም የምንገነባበት ግዜ ነው። በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የውይይት ስፍራ የምንለይበት። መጥተን ህይወታችንን እንደ ህያው መስዋዕት የምናስቀምጥበት እና ጌታ መጥቶ በሀይል እንዲሞላን የምንጋብዝበት ስፍራ።ልክ የድንጋዩ ካብ እኛን በትዕግስት ሲጠባበቀን እንዳገኘነው ሁሉ፣ የሚጠብቃቹ መሰውያ አለ። ስለዚህ ተነሱ፣ ሌላ ድንጋይ ጨምራቹ ካቡ፣ ለአንድ ተጨማሪ ግዜ ጸልያቹ እግዚአብሔር ዳግመኛ እንዲነሳ ተጠባበቁ።
Copyright Hiyawkal © 2024
Leave a Reply