በእግዚአብሔር የጸሎት ኦርኬስትራ ውስጥ እያንዳንዳችን የምንጫወትበት የራሳችን ቦታ አለን። በዚሀ ኦርኬስትራ ውስጥ የእናንተ ቦታ የቱ ጋር ነው? የትኛውን መሳሪያ ነው እናንተ የምጫወቱት? መንፈስ-ቅዱስ ደግሞ ይህንን መለኮታዊ ትርኢት እንደ እግዚአብሔር ቃል ይመራዋል።
እኔ አስራሁለት ያህል የተለያዩ የጸሎት አይነቶችን ለይቻለሁ። ከነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በእናንተ ጸሎት ውስጥ ተካትተዋል?
1. ስላደረገልን ምስጋና
የምስጋና ጸሎቶች በመንፈሳዊው ትርኢት ውስጥ በመጀመሪያው ረድፍ ይገኛሉ። ወደ አምልኮ እና ምልጃም ይመሩናል። መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፥ “ወደ ደጆቹ በመገዛት ግቡ፤”(መዝሙር 100፥4) ያንን ነው የምናደርገው። ለአመስጋኙ ለምጻም የሆነለትም ይህ ነበር።(ሉቃስ 17፥11-19)
በብሉይ-ኪዳን ለምጻሞች “ርኩስ ርኩስ ነኝ” በማለት እየጮሁ ከሌሎች ይለዩ ነበር። (ዘሌዋውያን 13፥45) አስሩ ለምጻሞች ግን ይፈውሳቸው ዘንድ ወደ ኢየሱስ ቀረቡ፤ ዘጠኙ ከተፈወሱ በኋላ ባለማመን እና በመገረም ሲሄዱ አንዱ ግን በሃይሉ የፈወሰውን መምህር በቀጥታ ሊያመሰግን ተመለሰ። ለዚህኛው ሰው ነው አመስጋኝ ልቡ፥ ለበለጠ ነጻነት፣ ደስታ፣ እና ፈውስ መንገድ የከፈተለት። ሌሎቹ ከለምጻቸው ነጹ፤ እርሱ ግን ሙሉ ፈውስን አገኘ። ኢየሱስ እንዲህ ነበር ያለው፥ “እምነትህ አድኖሃል” (ሉቃስ 17፥19) ምስጋና የሙሉ እና የጤናማ ሰው አስፈላጊ ባህሪ ነው።
2. ስለታላቅነቱ ምስጋና
“ወደ ደጆቹ በመገዛት ” ካለ በኋላ የሚመጣው “ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤” የሚል ነው። (መዝሙር 100፥4) ስላደረገልን ምስጋና ማቅረብ እና ስለታላቅነቱ ምስጋና ማቅረብ አንድ አይደሉም። ቅደም ተከትል አላቸው። በመጀመሪያ ስለመልካምነቱ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን። “እግዚአብሔር ቸር ነውና”(ቁጥር 5) ከዛም ስለታላቅነቱ እናመሰግነዋለን፤ “እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰው ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው።” (መዝሙር 48፥1)። እግዚአብሔርን ስለታላቅነቱ ማመስገን በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ትላቅ መሳሪያ ነው። ምስጋና የእስር ቤት በሮችን ከፍቶ እስረኞችን ነጻ አውጥቷል።
3. አምልኮ
ከምስጋና ቀጥሎ የምንሄደው ከልብ ወደ ሆነ አምልኮ ነው። ምንም እንኳን እነዚህን የጸሎት አይነቶች ከኦርኬስትራ መሳሪያዎች ጋር እያስተያየሁ ቢሆንም እውነታው ግን አምልኮ በአሁን ዘመን ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደሚታየው ሙዚቃ ብቻ አይደለም ይልቅስ ውስጣዊ የሆነ የልብ አቋም እንጅ። አምልኮ ዝቅ ማለት፣ መንበርከክ፣ እና ራስን ማዋረድ ነው።
መዝሙር 95 በመጀመሪያዎቹ ቁጥሮቹ ላይ እንደሚያበረታታን ስለእግዚአብሔር ታላቅነት አምልኮ “በእልልታ” ልንጀምር እንችላልን። ፍቃዳችንን የሚገልጠው አምልኮአችን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል። ብሎም ራሳችንን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ወደ መስጠትም ሊመራን ይችላል። አምልኮ በዌስትሚንስተር አጭር ጽሁፍ የመጀመሪያ ነጥብ ላይ እንደሰፈረው “የሰው የመጨረሻ ግቡ ነው” አምልኮ በሚሰማ የሙዚቃ ኖት ሆነም አልሆነም ለእመነታችን መሰረት ነው።
4. ራስን መለየት
እስካሁን ካልናቸው ቀጥሎ ራሳችንን ለእግዚአብሔር እናቀርባለን። “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።” (ሮሜ 12፥1) ይህ በዮሃንስ 17 ኢየሱስ በሊቀ ክህንነት ስለ እኛ እንደጸለየው ለእግዚአብሔር መቀደስ እንድንችል ያደርገናል። ወደ እግዚአብሔር አብ እንዲህ ነበር የጸለየው፥ “እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።”(ዮሃንስ 17፥19)
ራሳችንን ለእርሱ እየለየን ስንጸልይ ይህ ለጌታ ጆሮዎች ደስ የሚያሰኝ ነው። “አድነን” እያልን ስንጸልይ መስማትም ያስደስተዋል፤ ራሳችንን እየለየን ስንጸልይ የራስችን እንዳልሆንን በዋጋ የተገዛን መሆናችንን እንዳወቅን አና እንደተረዳን ያሳየዋል። ይህ “እኔን እና የእኔ የሆነውን ሁሉ አሳልፌ ሰጥቻለሁ” የሚለው ጸሎት በጸሎት ኦርኬስትራ ውስጥ ያስተጋባል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ መሪ እና ጌታ ነው።
5. አሳልፎ መስጠት
ስንቀጥል ራስን የመለየት ጸሎት አሳልፎ ወደመስጠት ጸሎት ይመራናል፤ መዝሙረኛው እንዳለ እንዲህ እንላለን “በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል።”(መዝሙር 31፥5) ራሳችንን ለእርሱ አሳልፈን ስንሰጥ በእርሱ ላይ በመታመን እንደገፋለን። እርሱም በሕይወታችን ትንሽ ስለምትመስለው ነገር እንኳን ሳይቀር ይጠነቀቅልናል። “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል።”(መዝሙር 37፥5)
አሳልፎ መስጠት ድርጊት ነው፤ መታመን ደግሞ ይልብ አቋም። ሸክማችሁ በከበደባችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ለጌታ አሳልፋችሁ ስጡት። (1ጴጥሮስ 5፥7 ይመልከቱ) ለእርሱ አሳልፋችሁ ስጡት፣ ከዛም ለእርሱ ጥላችሁት ሂዱ፤ ለእርሱ ከሰጣችሁ በኋላ ለእርሱ ተዉለት።
6. ልመና
ብዙ ጊዜ አሳልፈን ከመስጠትም በተጨማሪ የልመና ጸሎትንም እንጸልያለን። እንደእግዚአብሔር ፍቃድ የጸለይነው ጸሎት እንደሚመለስ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።” (1 ዮሃንስ 5፥14) የእግዚአብሔር ፍቃድ፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር መንገድ።
ስትጸልዩ፥ እንደቃሉ ነው የምትጸልዩት? “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።” (ማርቆስ 11፥24) ይህ ማለት የፈለከውን ነገር ሁሉ ታገኛለህ ማለት አይደለም፣ ይልቅስ በሚጨምር ቅድስና በተጓዝክ ቁጥር ፍላጎትህ እንደ ፍቃዱ ይሆናል ማለት እንጅ።
7. ምልጃ
የምልጃ ጸሎት ላይ ደርሰናል (ይሄ “ኢላማን መምታት” የሚለው መጸሃፌ ዋና ሃሳብ ነው።) እነዚህ ያየናቸው ጸሎቶች ሁሉ ይሰሙ ዘንድ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እንገባ ዘንድ ወደ አደባባዮቹ በምስጋና መግባት ያስፈልጋል።
ምልጃ ፍጹምነት በሚጎድለው የሰው ልጅ እና ፍጹም በሆነው አምላክ መካከል በመሆን የልመና ጸሎትን ስለሌሎች የምናደርስበት ነው። የሌሎችን መተላለፍ የእኛ እንደሆነ አድርገን በመናዘዝ የእግዚአብሔርን ምህረት እንጠይቃለን። (ኢሳይያስ 59፥2 15 ይመልከቱ) ስለሌሎች በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንዴት መታደል ነው፤ ምን አይነትስ የፍቅር ተግባር ነው!
8. ንስሃ
ሃዋሪያው ያዕቆብ እንዲህ ብሎናል “ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል።” (ያዕቆብ 2፥13) የንስሃ ጸሎት ሁል ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ጸሎት ነው። ከምናስበው በላይ ከባድ ብሎም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ፥ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ ምህረትን መለመን ከቶ የማይቻል ነገር ነው።
“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” (ዕብራውያን 4፥16) ወደ ጸጋው ዙፋን በራሳችን ሰዋዊ አቅም መቅረብ ከቶ የማይቻል ነው። ከልብ በሆነ ምስጋና ፣አምልኮ፣ እና ራስን መስጠት ነው መቅረብ ያለብን። ያኔ የምህረት ልቡን መቀብል እንደ ሃሳቡም መጸለይ እንችላለን።
9. የትዕዛዝ ጸሎት
አንዳንድ ጊዜ “በድፍረት” የትዕዛዝ ቃላትን በማውጣት ኢያሱ ጸሃይ በገባኦን ላይ እንዳትጠልቅ እንዳዘዘው መጸለይ ያስፈልግ ይሆናል።(ኢያሱ 10፥12‑15 ይመልከቱ) ይህ አይነቱን ነገር ለማድረግ ታላት የሆነ የእምነት ስጦታ ይጠይቃል።
የትዕዛዝ ጸሎት በባህሪው የአዋጅ ጸሎት ነው። ምንም እንኳን በኦርኬስትራው ውስጥ ሁሌ የምንጠቀምበት መሳሪያ ባይሆንም እውነተኛ እና መጽሃፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ ማወቅ ግን ተገቢ ነው።
10. በረከትን የማወጅ ጸሎት
ብዙ ጊዜ በረከቶችን እያወጅን እንጸልያለን አንዳንድ ጊዜም ግልጽ የሆነ በረከትን። “እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም።” እያልን እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ በሰጣቸው የበረከት ቃላት ሌሎች መባረክም እንችላለን። ይህንን ቁልፍ ነጥብ አስታውሱ፥ ያለንበት መንግስት በቃል እና በንግግር የሚሰራ መንግስት ነው።
እግዚአብሔር ህዝቡን የሚባርከው እንደዚህ ነው፥ “እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።” (ዘኆልቁ 6፥27) በእምነት ስጦታ ተሞልታችሁ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ፣ ቃል፣ እና መንገድ የሆነን ነገር ስታውጁ ሁሉ ይቻላል! (ማቴዎስ 19፥26 ይመልከቱ)
11. ጥላትን የሚያስደነግጥ ጸሎት
የጨለማን ሃይል የሚያፈርስ እና የሚከለክል ጸሎት መጸለይ እንችላልን? ሰይጣን ስራውን እንዳይቀጥል ማሰር እንችላልን? ኢየሱስ ፍሬ ያላፈራችውን የበልስ ዛፍ ሲረግማት ጠውልጋም ስትሞት ይህንን እያሰየ ነበር። (ማቴዎስ 21፥18‑22 ይመልከቱ) ይህ የሚሆነው የትዕዛዝ ጸሎት ከጽድቅ እና እምነት ጋር ሲደመር ነው። ኢየሱስ ዛፊቱን ሲያያት ቅጠል እንጅ ፍሬ አላገኘባትም ነበር። ከውጭ ሲታይ ፍሬአማ በደንብ ሲመረመር ግን ፍሬ ቢስ መሆኑ ታዬ።
ይህ አይነቱ ጸሎት “ይበቃል፤ በቃ “ የሚል ነው። ይህ ጸሎት መድረግ ያለበት በጥበብ ነው። መንፈስን መለየትን እና እምነትን ይፈልጋል፤ መደረግ ያለበትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ማረጋገጫን ካገኘን በኋላ ነው።
12. የማያቋርጥ ጸሎት
በጸሎት ኦርኬስትራ የመጨረሻው ድምጽ የማያቋርጥ ድምጽ ነው። መብራት ቢጠፋም ኦርኬስትራው መጫወቱን አያቆምም። በሉቃስ መጽሃፍ ላይ የምናውቀው ምሳሌ አለ፥ ስለዛች ከማያቋርጥ ልመናዋ የተነሳ ፍርድ ስለተፈረደላት መበለት። (ሉቃስ 18፥1‑8 ይመልከቱ) ከዚህም በፊት ኢየሱስ የማያቋርጥ ልመናው መፍተሄ ስላስገግኘለት አንድ ወዳጅ ምሳሌን ተናግሮ ነበር።(ሉቃስ 11፥ 5‑8 ይመልከቱ)
ሳታቋጡ ጸልዩ፤ አታቁሙ። ብዙ ስተጸልዩ ወደ እግዚአብሔር ልብ የበለጠ መቅረብ ይሆንላችኋል። እኔ እና እናንተ የተጠራነው በዚህ በጨልማው አለም የብርሃንን መንግስት እናሰፋ ዘንድ ነው። ተስፋ መቁረጥ ምርጫችን ሊሆን አይችልም።
ምሳሌያዊ ጸሎት
ሁሉን የምትችል ጌታ እግዚአብሔር ሆይ የጻድቅ ሰው ጸሎት በስራዋ እጅግ ሃይልን ታደርጋልችና አመሰግንሃለሁ። እነዚህንም ጸሎቶች በመረዳቴ ላይ እጨምራለሁ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ የትኛውን የጸሎት መሳሪያ በትክክለኛው ጊዜ እና እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ ማወቅ እንድችል አንተ ምራኝ። ኢላማዬን መምታት የምችልባቸውን ጸሎቶች ስላስተማርከኝ በከበረው በክርስቶስ ኢየሱስ ስም አመሰግንሃለሁ። አሜን አሜን።
Copyright Hiyawkal © 2024
Leave a Reply