ሦስቱ ጉልቻ

ሦስቱ ጉልቻ _ እንዳለ ገብረመስቀል ብርሃን መፅሔት 1989 ቁጥር 27 :

ሦስቱ ጉልቻ ፣ ድርብ ጋብቻ ፣ የጋብቻ ትርጉም

ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የሚቀራረቡበት የሚዋደዱበትና በአካል አንድት የሚኖሩበት ግላዊ ግንኙነት ሲሆን በዘመነናቸው በሚያሳዩት የጋራ ፍቅርና በሚገቡት ቃለልኪዳን እያደገ የሚሄድ ጓደኝነት ነው ክርስቲያናዊ ጋብቻ በእግዚአብሄር ቃል በአዋቂዎች ምክርና በኅብረተሰብ ሕጎች እየተጠበቀ የሚቀጥል ማኅበራዊ ተቋም ነው፡፡

የጋበቻ አመሰራረት

ጋብቻ የተመሰረተው በእግዚአብሔር ነው፡፡ ከሰው ጋር አብሮ የተፈጠረ ተቋም ሲሆን ሰውም የተፈጠረው ለጋብቻ ነው (ዘፍጥ.1፡-26-27፤2፤18-25)፡፡ ከዚህ ሁነት አያሌ ዘመናት በኋላ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ካሳያቸው ካጠናከራቸው ነገሮች
አንዱ የጋብቻን ክቡርነት መግለጽ ነበር (ማቴ.19፤3-12)፡፡ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው መጠን መጋባት ንፁህና ቅዱስ እንዲሆን በትምህርታቸውና በምሳሌነታቸው ጠብቀው አቆይተዋል (ኤፌ.5፤21-33፤ዕብ.13፤4)፡፡

የጋብቻ ብልሽት
ጋብቻ ከመሰረቱ በእግዚአብሔር የተቀደሰ ሆኖ ሳለ ሰው በኃጢያት ከወደቀ በኋላ የውድቀት ውጤት በጋብቻም ላይ ተንፀባርቋል፡፡ የተለያዩ ጉድለቶችም የደረሱበት ሲሆን እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • 1. ደርብ ጋብቻ ፡-ዘፍጥ.4፤19፣23
    2. አመንዝራነት ፡-ዘፍጥ.16፤1-6
    3. ግብረሰዶም ፡- ዘፍጥ.19፤4-11
    4. አስገድዶ መድፈር ፡ዘፍጥ.34፤12
    5. ግልሙትና፡- ዘፍጥ.38፤1-30
    6. ሴሰኝነት ፡-ዘፍጥ.39፤7-13

እግዚአብሔር አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፈጠረ ሲሆን ሁለቱም ሲጣመሩ አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ የጋብቻ ሚስጥር በዘመናት ሁሉ እንዲጠበቅ የእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በኃጢያት ምክንያት በጋብቻ ላይ ከተከሰቱ ብልሽቶች አንዱ ድርብ ጋብቻ ሆነ፡፡ ድርብ ጋብቻ ከሁለት በላይ የትዳር ባልንጀሮችን ያቀፈ የጋብቻ አይነት ነው፡፡ አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሚስቶች ያገባበትን ወይንም አንዲት ሴት ከአንድ በላይ ከሆኑ ባሎች ጋር የምትኖርበትን የጋብቻ ሁኔታ ይመለከታል፡፡
ድርብ ጋብቻ በተመሳሳይ ጊዜ ከአንድ በላይ ከሆኑ የትዳር ባልንጀሮች ጋር መኖርን ሲያመለክት አንዳንድ ጊዜ በማግባት በመፍታት ዑደት በማያቋርጡ የድርብ ጋብቻ ሂደት ውስጥ መገኘትንም ያመለክታል፡፡

ድርብ ጋብቻ ባህላዊ መንስኤዎች

ከወንዶች ይልቅ የሴቶች አኃዝ መብዛት
ብዙ ለማግባት የሚደረግ ባላዊ ተፅእኖ
ብዙ ልጆች ለመውለድ ያለ ናፍቆት
የሟች ወንድም ሚስትና ሐብት እንዲወረስ የሚደረግ ባህል
ሴቶች ጡት በሚያጠቡበት ጊዜ ከሩካቤ ስጋ ራሳቸውን እንዲያገሉ የሚያደርግ ባህልና ወግ
የመጀመሪያ ሚስት ታማሚ መሆንና በእድሜ መግፋት
የወንዶች የፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ከሴቶች ይልቅ ጠንካራ ነው የሚል ልማዳዊ አስተሳሰብ
በእርሻ የሚተዳደሩ ኅብረተሰቦች ከፍተኛ ጉልበት መፈለግ(ምግብ እንደልብ እንዲገኝና ልጆቸችም በብዛት ተወልደው ሥራ እንዲያግዙ)
ሚስት ለማግባት የሚከፈል ጥሎሽ ባለበት ባህል የብዙ ሚስቶች ባል መሆን እንደ ባለጠጋ ማስቆጠር፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆ

ሀ. እግዚአብሔር ከጥንት ከመሰረቱ በጋብቻ ያጣመረው አንድ ወንድና አንዲት ሴትን ብቻ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለጋብቻና ፍቺ ባስተማረ ጊዜ ሰዎች ከልባቸው ጥንካሬ የተነሳ የእግዚአብሔርን ሕግ ለማላላት ቢሞክሩም መሠረቱ ግን አንድ ወንድና አንዲት ሴት ብቻ የሚጣመሩበት ኅብረት እንደሆነ አጽንቷል፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ጋብቻ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን ውኅደት ምሳሌ እንደሆነ ምስጢሩ ተገልጦለታል (ዘፍጥ.2.፤24፤ማቴ.19፣2-10፤ኤፌ.5.፤21-33)፡፡

ለ. ድርብ ጋብቻ የተጀመረው ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ ሲሆን ጀማሪውም የክፉው የቃየን ዘር የሆነው ላሜህ ነው(ዘፍ.4፤19)፡፡ የእስራኤል አባቶችና መሪዎች የሆኑት አብርሃም ፣ያዕቆብ፣ ዳዊት ፣ሰለሞንና ሌሎችም በድርብ ጋብቻ ውስጥ ይኖረዋል፡፡ ይህ ድርጊታቸው ከእግዚአብሔር የጋብቻ ጽንስ ሐሳብ ጋር ግን ተጻጻራሪ ነበር፡፡ በአንድ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር ሲታገስ ነገሩ የእርሱ ፈቃድ ስለሆነ ነው ብለን መናገር አንችልም፡፡ ድርብ ጋብቻ በሕይወታቸው ከማለፉም የተነሳ ቤተሰብ ውዝግብና የኑሮ ቀውስ ተፈጥሮባቸዋል፡፡ አዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች በስህተታቸው ልንገሠጽ እንጂ ልታነጽ አይገባም (ዘዳግ.17፤17፤1ቆሮ.10፣11)፡፡

ከድርብ ጋብቻ ጋር የማይጣጣሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆዎች

በፍጥረት ጊዜ የተደነገገውን አምላካዊ የጋብቻ ሕግ ይጻረራል (ዘፍጥ.2.፤24)፡፡
የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ሆነውን ሰውነት በዝሙት ያፈርሳል(1ቆሮ.6፤12-20)፡፡
በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን የውኅደት ምሳሌ ያፈርሳል(ኤፌ.5፤21-33)፡፡
በክርስቶስ የሕይወትን ጸጋ ከሌሎች ጋር አብረው በእኩልነት እንዲወርሱ የተጠሩ ሚስቶችን ዝቅ ያደርጋል (1ጴጥ.3፤7)፡፡
ከአንድ በላይ ማግባት ትክክል ያልሆነና ገደብ የለሽ ልቅነትና ርኩሰት ያስከትላል (ሉቃ.17.፤27-29፤ዕብ.13፤4)፡፡

የቤተክርስቲያን የመፍትሔ ሐሳቦች

ድርብ ጋብቻ በአገራችን በኢትዮጵያ በበርካታ ብሔረሰቦችና በአንዳንድ የሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ በአፍሪካ አህጉርም በብዙ አገሮች ያለ ልማድ ነው፡፡ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት በወንጌል ስርጭት ውጤት ተገኝተው የድርብ ጋብቻ ሕይወት የሚኖሩትን ለማስተናገድ ብዙ መፍትሔዎችን ሞክረዋል ከወሰዱትም መፍትሄዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

በአባላት ለመታቀፍ ወንዶች የመጀመሪያ ሚስታቸውን እንዲያስቀሩትና ሌሎቹን እንዲፈቱ ማድረግ፡፡
የሚወዷትን አንዷን ብቻ በማስቀረት ሌሎቹን መፍታት፡፡
በዕድሜ የገፋችውን ሚስት ማግለልና ልጅ እግር ከሆነችው ጋር እንዲቆይ ማድረግ፡፡
ባል ለቀሩት ሚስቶች ሐብት ንብረት አካፍሎ መንከባከብና ከሩካቤ ሥጋ ግን ራስን በማግለል ከአንዷሚስት ጋር መወሰን፡፡
የተፈቱት ሚስቶች ክርስቲያን ባሎች እንዲያገቡ ማመቻቸት፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት የመፍትሔ ሐሳቦች ብዙ ደካማ ጎን ያላቸውን ሲሆን አንዳንዶቹም የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎችን ይጻረራሉ (ሚል.3፤16፤ማቴ.19፤9) የቤተሰብ አንድነትንና የልጆች እድገትና ያናጋሉ የወንዱን ጥቅም ብቻ ያስጠብቃሉ የእግዚአብሄርን የይቅርታ ትርጉም ያዛባሉ የድርብ ጋብቻ ባህልና ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ክርስቶስ ወንጌል እንዳይደርሱም በር ይዘጋሉ፡፡

ድርብ ጋብቻና የድኅነት (ደኅንነት) ወንጌል

ሀ. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም ስለሞተ በድርብ ጋብቻ ላሉትም ሰዎች ሕይወቱን አሳልፎ ሰቷል፡፡

ለ. ድኅነት የግል ውሳኔ በመሆኑ በድርብ ጋብቻ ውስጥ ያሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ኢየሱስ ክርስቶስን የግል መድኃኒታቸው አድርገው ከወሰኑ ይድናሉ፡፡

ሐ. ባለማወቃቸው ወራት ካደረጉት ሁሉ በንስሀ እስክትመለሱ ድረስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቀበላቸዋ፡፡ ጌታ ከተቀበላቸው ቤተክርስቲያንም ልትቀበላቸው ይገባል፡፡

መ. የንስሐ ዕድል የንስሐ ፍሬም ያስፈልገዋል፡፡ በድርብ ጋብቻ እየኖሩ ሳሉ በንስሐ ጌታን በማመን የተመለሱ የንስሐ ፍሬ የሚያሳዩት ሚስቶቻቸውን በመፍታት ሊሆን አይችልም፡፡ ዳሩ ግን ደግመው ወደዚህ ዓይነቱ ኑሮ እንዳይመለሱና ሚስቶችን
በመጨመርም ሆነ በመፍታት እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ ትምህርትና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ሠ. በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው መዳን ከቻሉ በግል ውሳኔያቸው በውሃ መጠመቅ ይችላሉ፡፡ ባልና ሚስት አብሮ መጠመቁ የሚደገፍ ቢሆንም የጥምቀት መስፈርት የጋብቻ አቋምን አይጠይቅም(ማር.16፤16) የሐዋ. 2፤41- 42፤16፤31)፡፡

ድርብ ጋብቻና የአማኞች ቅድስና

አማኞች ክርሰቲያናዊ ጋብቻ በጌታ በሆኑ አንድ ወንድና አንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚደረግ ኅብረት መሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡

የትዳር ባልንጀራ በሕይወት ሳለ ጋብቻን መደረብ በአማኝ ዘንድ አመንዝራነት ነው(ሮሜ 7.፤1-3)፡፡

የቤተክርስቲያን አባል ሆነው ጋብቻን በሚደርቡ ሰዎች ላይ ቤተክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ልትወስድ ይገባታል፡፡

ከአለማወቅና ካለማመን ከኖሩበት ኑሮ በንስሐ የተመለሱትንና ቤተክርስቲያን የተቀበለቻቸውን በማየት ታንፀው በድርብ ጋብቻ እንዳይወድቁ አማኖችን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

ድርብ ጋብቻና አገልግሎት

ሀ. ድርብ ጋብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስላይደለ በእግዚአብሔርም ሆነ በቤተክርስቲያን የሚደገፍ አይደለም፡፡

ለ. በቅድመ ክርስቲያን ኑሯቸው በድርብ ጋብቻ የተያዙ ቤተሰቦች በንስሐ ተመልሰውና ታድሰው በእግዚአብሔር መንግስት ዜጎቸችና የቤተክርስቲያን አባላት መሆን ቢችሉም የቤተክርስቲያን መሪዎች ግን መሆን አይችሉም (1ጢሞ.3፤2፤ቲቶ1፤6)፡፡

ሐ. ለእረኞች የተሰጠው መሪ ቃል ‹‹ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ›› የሚል ሲሆን በጋብቻ አቋማቸውም ምሳሌያዊ የሆነውንና በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚደረገውን ጋብቻ የሚኖሩ መሆን አለባቸው ድርብ ጋብቻ ምሳሌያዊ ጋብቻ አይደለምና፡፡

ማጠቃለያ

ድርብ ጋብቻ በዓይነቱ ብዙና የተወሳሰበ ነው፡፡ ሁሉንም የድርብ ጋብቻ ችግሮች በዚህ ጽሁፍ ማንሳትና ማስተማር ያዳግታል፡፡ በዚህ ጽሁፍ የቀረቡት አስተያየቶች የጽኁፍ አቅራቢው የግል መረዳቶች ናቸው፡፡ ይህን በመሰለ የአንድ ሰው አስተያየትም ወጥና ዘላቂ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ግለሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት በትምህርት በጥናትና በልምድ የዳበረ አስተያየታቸውን ለድርብ ጋብቻ ችግር እንዲያስተባብሩ ያስፈልጋል፡፡ የሚከተሉትም ነጥቦች አብያተ ክርስቲያናት በተጠናጠልም ሆነ በጋራ ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ መንገዶች እንደሆኑ አስባለሁ፡፡

የድርብ ጋብቻ ጉዳይ በአካባቢያዊ ብሔራዊና አህጉራዊ ደረጃ ማጥናት፡፡

በድርብ ጋብቻና በሌሎችም ጋብቻ ነክ ችግሮች ላይ በጉባኤ መምከር፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግና የኅብረተሰቡን ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለድርብ ጋብቻ ጉዳይ የሚጠቅሙ ወጥ የሆኑ መመሪያዎችንና ደንቦች ማውጣት፡፡

በጋራ በተደረሱ ስምምነቶችና ውሳኔዎች ላይ በመመስረት የቤተክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮችን ግንዛቤ ማስጨበጥ፡፡

አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በአንድ ሐሳብ ተስማምተው የድርብ ጋብቻን ጉዳይ የሚፈቱበትን ደንቦችና መመሪያዎች ማሰራጨትና መከተል፡፡

ገንቢ የሆኑ አዳዲስ የመፍትሄ ሐሳቦችን በልበ ሰፊነት በማስተናገድ በየጊዜው ነባር ደንቦችን መገምገምና ማሻሻል፡፡

በተመሳሳይ ባህላዊ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትና አገሮች ልምድ መማር፡፡

እንዳለ ገብረመስቀል
ብርሃን መፅሔት
1989 ቁጥር 27

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Follow by Email
YouTube
YouTube
Set Youtube Channel ID
Telegram

ማሕደር

Language
WordPress Image Lightbox